Tuesday, July 30, 2013

የአብርሃም ዛፍና የአብርሃም ድንኳን

በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ
ነገረ ማርያም በብሉይ ኪዳን ከሚለው መጽሐፍ የተወሰደ 



እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እግዚአብሔር ለአብርሃም በአንድነት በሦስትነት በተገለጠባት ዛፍና፤ በገባበት ድንኳን ትመሰላለች (ዘፍ ፲፰፥፩-፴፫)፡:

ይኸውም አብርሃም ከደግነቱ ብዛት እንግዳን ከመውደዱ የተነሣ ድንኳኑን በተመሳቀለ ጎዳና ሠርቶ የወጣ የወረደውን ያለፈ ያገደመውን ሲቀበል የሚኖር በሥራው ኹሉ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ጻድቅ ነበር (ሮሜ ፬፥፩-፫)፡፡ ጽድቁም ሊታወቅ ስድስት ሰዓት ላይ አብርሃም በድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ፤ በመምሬ ዛፍ ሥር እግዚአብሔር በአንድነት በሦስትነት ተገለጸለት ‹‹ወሶበ አልዐለ አብርሃም አዕይንቲሁ ነጸረ ሠለስተ ዕደወ እለ ይቀውሙ ወርእየ ወሮጸ ለተቀብሎቶሙ እምኆኅተ ኅይመት ወሰገደ ውስተ ምድር›› ይላል ዐይኑን አቅንቶ ሲመለከት፤ ሥላሴ በአምሳለ ዕደው ቆመው አይቶ፤ ሊቀበላቸው ከድንኳኑ ደጃፍ ተነሥቶ ሮጠ፤ ወደ ምድርም ሰገደ፤ ከዚኽ በኋላ ‹‹አቤቱ በፊትኽስ ሞገስ አግኝቼ እንደኾነ ባሪያኽን አትለፈኝ ብዬ እለምናለኍ፤ ጥቂት ውሃ ይምጣላችኍ፤ እግራችኹን ታጠቡ፤ ከዚኽችም ዛፍ በታች ዕረፉ…›› በማለት ተናግሯል፡፡ ‹‹በፊትኽ ሞገስን አግኝቼ›› ብሎ አንድነታቸውን፤ ‹‹ውሃ ይምጣላችኍ›› ብሎ የሦስትነታቸውን ምስጢር ገልጾአል፡፡

ይኽቺ አንድነቱ ሦስትነቱን ሳይጠቀልለው ሦስትነቱ አንድነቱን ሳይከፍለው በአንድነት በሦስትነት የሚመሰገን እግዚአብሔር የተገለጠባት ዛፍ፤ አንድነት ሦስትነት በጐላ በተረዳ ነገር የታወቀባት ከሦስቱ አካል አንዱ አካል እግዚአብሔር ወልድን በድንግልና የወለደች የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ መኾኗን፤ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ እንዚራ ስብሐት መጽሐፉ ላይ
....‹‹አንቲ ውእቱ ዕፀ ድርስ ዘለአብርሃም በርስአኒሁ
....ዘብኪ አጽለለ እግዚአብሔር በሥላሴሁ ››
(ለአብርሃው በእርጅናው ወቅት፤ እግዚአብሔርን በሦስትነት ያስጠለለብሽ የወይራ ዕንጨት አንቺ ነሽ) በማለት ሲገልጥ፤ ዳግመኛም በዚኹ መጽሐፉ፡-

...‹‹እንቲ ውእቱ ዕፀት ዘነበርኪ ጥቃ ኀይመት፣
...ዘብኪ አጽለሉ ሠለስቱ አጋዕዝት››
(ባንቺ ሦስቱ ጌቶች (ሥላሴ) የተጠለሉብሽ በድንኳን አጠገብ የቆምሽ ዕንጨት አንቺ ነሽ) በማለት በአንድነቱ ምንታዌ (ኹለትነት)፣ በሦስትነቱ ርባዔ (አራትነት) ለሌለበት አምላክ የሦስትነቱ የአንድነቱ ምስጢር መገለጫ የሥላሴ ማደሪያ መኾኗን መስክሯል፡፡


ይኸውም ጌታ ከእመቤታችን ከመወለዱ አስቀድሞ የአንድነት የሦስትነት ምስጢር እምብዛም በጐላ በተረዳ ነገር አይታወቅም ነበር፤ “ወአልቦ ዘአእመሮሙ ለሥሉስ ቅዱስ መኑሂ ዘእንበለ እምድኅረ ተሠገወ ወልድ ዋሕድ እምቅድስት ድንግል” እንዳለ ሊቁ አንድነት ሦስትነት በጐላ በተረዳ ነገር የታወቀው ጌታ ከእመቤታችን ከተወለደ ወዲኽ ነው (ሉቃ ፩፥፴፬‐፴፭፤ ዕብ ፩፥፩‐፪)፡፡

ከዚኽም ምስጢር የተነሣ አብርሃምም ሳራን “ሦስት መስፈሪያ የተሠለቀ ዱቄት ፈጥነሽ አዘጋጂ፤ ለውሺውም እንጎቻም አድርጊ” በማለት የተገለጸለትን የሦስትነት የአንድነት ምስጢርን አጒልቶ ተናግሯል፡፡ ጌታም አብርሃምን ‹‹የዛሬ ዓመት እንደዛሬው ጊዜ ወደ አንተ በእውነት እመለሳለኍ፤ ሚስትኽ ሳራም ልጅን ታገኛለች›› በማለት ዘመኑ ሲፈጸም ከቤተ አብርሃም ከተገኘች ከእመቤታችን የመወለዱንና፤ በሳራ የተመሰለች ወንጌል ምእመናንን እንደምታስገኝ በምስጢር ገልጾለታል፤ ቅዱስ ጳውሎስም አካላዊ ቃል በሰጠው ተስፋ መሠረት ከነገደ አብርሃም የመወለዱን ነገር ለዕብራውያን ሰዎች በጻፈው መልእክቱ ላይ (በሕይወታቸው ኹሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ኹሉ ነጻ እንዲያወጣ፤ በሥጋና በደም እንዲኹም ተካፈለ፣ የአብርሃምን ዘር ይዞአል እንጂ የያዘው የመላእክትን አይደለም) በማለት ገልጾታል (ዕብ ፪፥፲፭-፲፮)፡፡

ይኽቺ ሥላሴ የገቡባት ኀይመተ አብርሃም (የአብርሃም ድንኳን) የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ናት፤ ይኸውም ሥላሴ ወደ አብርሃም ድንኳን እንደገቡ ኹሉ፤ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያምም፤ አብ ለአጽንኦ፣ መንፈስ ቅዱስ ለአንጽሖ፣ ወልድ በተለየ አካሉ ሥጋን ለመዋሐድ ዐድረዋል (ሉቃ ፩፥፴፭)፤ በመኾኑም አማናዊቷ የሥላሴ ማደሪያ የአብርሃም ድንኳን እመቤታችን ብቻ ናት፡፡

ሊቁም በነገረ ማርያም ይኽነን ምስጢር ሲገልጽ ‹‹ወይእቲ ኀይመት ትትሜሰል በድንግል ወዕደው አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ እሙንቱ፤ አብ አጽንኣ፣ ወወልድ ተሰብአ እምኔሃ፣ ወመንፈስ ቅዱስ ቀደሳ ከመ ትጹር አምላከ በከርሣ›› (ያቺ ድንኳንም በድንግል ትመሰላለች፤ ሰዎቹም አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ናቸው፤ አብ አጸናት፣ ወልድም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ሰው ኾነ፣ መንፈስ ቅዱስ አካላዊ ቃል አምላክን ትሸከም ዘንድ ለያት) በማለት ሲተረጒም፤ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ በሰላምታ መጽሐፉ ላይ መጽሐፉ ‹‹ኀይመተ አብርሃም አብ ሰላም ለኪ፤ ዘኮንኪ ከመ ተድባብ ሰላም ለኪ›› (እንደ ጥላ የኾንሽ የአባት አብርሃም ድንኳን ሰላምታ ይገባሻል) በማለት አመስግኗታል፡፡

ይኽ አብርሃም የተቀበለውን የተስፋ ቃል ሊቃውንት ሲተረጒሙት ‹‹ኦ አኃውየ በይነ መኑ እንከ ዘይቤ እግዚአብሔር ለአብርሃም አመ ከመ ዮም እገብእ ኀቤከ አኮኑ እግዝእትነ ማርያም ይእቲ ዘወፅአት እምነ ሥርው ለአዳም ወእምነ ሐቌሁ ለኖኅ ወፈለሰት ውስተ ቤተ አብርሃም አበ ብዙኃን ዘበእንቲአሃ ተአንገዱ ሥላሴ ውስተ ቤተ አብርሃም ለዜንዎ ትሥጉተ ወልደ እግዚአብሔር እምነ ዘርዑ ለአብርሃም፤ ወበእንተዝ ይደልወነ ንለቡ ናእምር ከመ ያስተርኢ እግዚአብሔር ትእምርተ ሥርወ ልደታ ለእግዝእትነ በበጊዜሁ›› (ወንድሞቼ ሆይ እግዚአብሔር አብርሃምን እንደዛሬው ኹሉ ወደአንተ ተመልሼ እመጣለኍ ያለው ስለማን ይመስላችኋል? ከአዳም ሥር ወጥታ፤ ከኖኅ አብራክ ተገኝታ፤ ወደ አብርሃም አብራክ ልትከፈል፤ ሥላሴ በአብርሃም ቤት በእንግድነት ተገኝተው፤ ከአብርሃም ዘር ከእመቤታችን የእግዚአብሔርን ልጅ ሰው መኾን ስለርሷ የተናገሩላት እመቤታችን ድንግል ማርያም አይደለችምን፤ ስለዚኽ እግዚአብሔር ስለ እመቤታችን ጥንታዊ የልደቷን አመጣጥ በየጊዜው ምልክት እንደሚሰጥ ልብ አድርገን ማስተዋል ይገባናል) በማለት አብራርተው ተርጒመዋል፡፡

ሊቁ አባ ሕርያስቆስም በቅዳሴው በቊ፴፪ ላይ ‹‹ተናግዶቱ ለአብርሃም›› (የአብርሃም እንግድነቱ አንቺ ነሽ) በማለት ምስጢሩን ጠቅልሎ የገለጠውን ይኽነን ድንቅ ምስጢር፤ ሊቁ በነገረ ማርያም ላይ በስፋትና በጥልቀት፡- ‹‹ወዓዲ ኀይመት ዘአብርሃም ዘውስቴታ ተአንገደ እግዚአብሔር አኮ ከማሁ ዘኮነቶ ምጽላለ በእንተ ምዕር አላ ኮነቶ እመ ወተከድነ ሥጋሃ ወረሰዮ አሐደ ምስለ መለኮቱ›› (ዳግመኛም እግዚአብሔር (በሦስትነት) በዕንግድነት ያረፈባት የአብርሃም ድንኳን አንቺ ነሽ፤ ለጥቂት ጊዜ ብቻ መጠለያን፣ መጠጊያን የኾነቺው አይደለም፤ እናትን ኾናው ሥጋዋን ተዋሕዶ ከመለኮቱ አንድ አደረገው እንጂ) በማለት በአብርሃም ድንኳን ብትመሰልም እንኳ ክብሯ ከፍ ያለ፤ ለዘላለም የአምላክ ማረፊያውና እናቱ መኾኗን አብራርቶ ገልጧል፡፡

በተጨማሪም አምላክን በአንድነት በሦስነት ለማየት ለበቃ ለደጉ አብርሃም አስቀድሞ ‹‹የምድር ነገዶች ኹሉ በአንተ ይባረካሉ›› (ዘፍ ፲፪፥፫) በማለት የገባለትን የተስፋ ቃል፤ በድንኳኒቱ ውስጥም “የዛሬ ዓመት እንደዛሬው ጊዜ ወደ አንተ እመጣለኍ” በማለቱ ከርሱ ወገን ከኾነች ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለዱን ገልጾለት፤ ያውም ከገረዲቱ ከአጋር ልጅ ከይስማኤል ሳይኾን፤ ከእመቤቲቱ ልጅ ከሳራ ልጅ ከይስሐቅ ዘር ከተገኘች ከድንግል ማርያም አካላዊ ቃል ስለመወለዱ ‹‹እስመ እምይስሐቅ ይሰመይ ለከ ዘርዕ›› (በይስሐቅ ዘር ይጠራልኻል) በማለት አጕልቶ ነግሮታል (ዘፍ ፳፩፥፲፪-፲፫፤ ሮሜ ፱፥፯-፲፫)፡፡


የአብርሃም ድንኳን ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ ባርኪኝ

No comments:

Post a Comment