Sunday, April 28, 2013

ሰሙነ ሕማማት


መምህር ኃይለ ማርያም ላቀው

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከትንሣኤ በፊት ያለውን አንድ ሳምንት ሰሙነ ሕማማት /የሕማማት ሳምንት/ በማለት ትዘክረዋለች፡፡ ሕማማት የሚለው ቃል “ሐመ፤ ታመመ” ከሚለው የግእዝ ግስ የወጣ ሲሆን የጌታችንና የመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕማምና ሞቱ የሚዘከርበት ሳምንት ነው፡፡ በሌላም በኩል ይህ ሳምንት ከአዳም እስከ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱሱ ክርስቶስ የነበሩ ነፍሳት በሲኦል የቆዩበት የአምስት ሺህ አምስት መቶ የመከራ፣ የፍዳና የኩነኔ ዘመን መታሰቢያ ስለሆነ የሕማማት ሳምንት የሚለውን ስያሜ አግኝቷል፡፡ እንደዚሁም ይህ ሳምንት “ቅዱስ ሳምንት” ይባላል” ከሌሎች ሳምንቶች ሁሉ የተለየ የከበረ ነውና፡፡ ምክንያቱም በዚህ ሳምንት በእያንዳንዱ ዕለት ስለ ፍጹም ፍቅር የተከፈለ የመሥዋዕትነት ሥራ ስለ ተሠራበት፣ የሰው ልጆች ደኅንነት ስለ ተፈጸመበት፣ መድኀኔዓለም ስለ እኛ ቤዛ ሆኖ ለመስቀል ሞት ታዛዥ ሆኖ ነፍሱን ስለ ካሠልን “ቅዱስ ሳምንት” ተብሏል፡፡ በተጨማሪም “የመጨረሻ ሳምንት” ተብሎ ይጠራል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም በሙዓለ ሥጋዌው ለፈጸማቸው የቤዛነትና የአርአያነት ተግባራት ፍጻሜ በመሆኑ ነው፡፡
በዚህ ልዩ በሆነ ሳምንት ካህናትና ምእመናን በነግህ፣ በሠልስት፣ በቀትር፣ በተሰዓትና በሠርክ ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመጓዝ ስለ ጌታችን ኢየስስ ክርስቶስ ሕማማተ መስቀል የሚያዘክረውን ምዕራፍ ከቅዱሳት መጻሕፍት በማንበብና በመጸለይ ሕማሙንና ሞቱን ያዘክራሉ፤ ቅዱስ ያሬድ በመጨረሻው ሳምንት በየዕለቱ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የተፈጸመውን ነገረ መስቀል በተመለከተ ያዘጋጀውን መዝሙር ይዘምራሉ፤ አብዝተው ስግደትን ይሰግዳሉ፡፡

Sunday, April 14, 2013

ገብርኄር


በዲ/ን አባተ አስፋ
ዛሬ ታላቁን የጌታችንን ጾም ከጀመርን ስድስተኛ ሳምንት ላይ ደርሰናል፡፡ ይህን ሳምንት ቅድስት ቤተክርስቲያን «ገብርኄር» የሚል ስያሜ ሰጥታዋለች፡፡ ገብርኄር በጎ አገልጋይ ማለት ሲሆን የስያሜውን መነሻ የምናገኘው በዕለቱ ሥርዓተ ቅዳሴ ከሚነበበው የወንጌል ክፍል ማቴ.25-14-30 ነው፡፡
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምሳሌ መስሎ ካስተማራቸው ትምህርቶች መካከል አንዱ የሆነው ይህ የዛሬው ወንጌል አስተማሪ የሆኑ መሠረታዊ ጉዳዮችን በውስጡ ይዟል፡፡ በተለይ ምንም እንኳን የቤተክርስቲያን ሓላፊነት የእገሌና የእገሊት ተበሎ ባይወሰንም ቤተ ክርስቲያን ባላት የአገልግሎት መዋቅር መሠረት የሓላፊነትን ቦታ ይዘው ለሚያገለግሉ ሰዎች አትኩሮት ሊሰጡባቸው የሚገባቸውን ነጥቦች ይጠቁማል፡፡ ይህን ለማየት ያመቸን ዘንድ ከታሪኩ የመጀመያ ክፍል በመነሣት ዋና ዋና የሆኑ ዐሳቦችን በአትኩሮት መመርመር ጠቃሚ ነው፡፡

Sunday, April 7, 2013

ደብረ ዘይት


በአባ ዘሚካኤል ደሬሳ
የዓለሙ ፍጻሜ ምልክቱ ምንድ ነው?/ማቴ. 24፣3/

በዓቢይ ጾም ውስጥ ካሉት ሳምንታት ደብረ ዘይት 5ኛው ሳምንት ላይ ይውላል፡፡ ደብረ ዘይት ትርጉሙ የወይራ ዛፍ ተራራ ማለት ሲሆን፣ ይህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኢየሩሳሌም በሚገኘው በደብረ ዘይት ተራራ ቅዱሳን ሐዋርያት” የዓለሙ ፍጻሜስ ምልክቱ ምንድነው?”/ማቴ. 24፣3/ ብለው ጠይቀውት እርሱም የማይቀረውን የዓለም ፍጻሜና አስቀድመው የሚፈጸሙ ምልክቶችን አስረድቷቸዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ይህንኑ በደብረ ዘይት ሳምንት ታስበዋለች፤ ለምእመናኑም ከዘመኑ ሁኔታ አንጻር በመጻሕፍት የተጠቀሱትን የትንቢት ምልክቶቹን ከተግባራዊ የዓለም ክንዋኔዎች አንጻር በማገናዘብ ታስተምራለች፡፡ በመሆኑም በቤተ ክርስቲያናችን በደብረ ዘይት ሳምንት ምጽአትን አስመልክቶ የሚነገሩ ምስጢራት እጅግ ሰፊ ናቸው፡፡ ነገር ግን በዚህ ጽሑፍ በመጠኑ የምናየው ከቅዱሳት መጻሕፍት አንጻር በዓለም እየተከሰቱ ካሉ ወቅታዊ ምልክቶች ጋር በማገናዘብ ይሆናል፡፡