Sunday, June 23, 2013

ጰራቅሊጦስ

በቤካ ፋንታ

  • እግዚአብሔር የሠራት ቀን ይህች ናት/ መዝ 118፥24/
ይህች ታላቅ ዕለት  ከቅድስት ሥላሴ አንዱ አካል የሆነው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ለቅዱሳን ሐዋርያት፣ ለቅዱሳን አርድእትና ለቅዱሳት ሴቶች የተገለጠባት ዕለት ናት፡፡    እነዚህ ሁሉ በጸሎት ተግተው በሚጸልዩበት ወራት መንፈስ ቅዱስ  በተከፋፈሉ የእሳት ልሳን አምሳል የወረደበት ቅዱስ ቀን ነው፡፡

አስቀድሞ ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱሳን ሐዋርያት ደብረ ዘይት በተባለ ታላቅ ተራራ ላይ ሳሉ እንዲህ ብሎ አስተምሯቸው ነበር “ኀይልን ከላይ ከአርያም እስክልክላችሁ ድረስ በኢየሩሳሌም በጸሎት ቆዩ፡፡”/ሉቃ 24፡36/ መቶ ሃያው ቤተሰብም በኢየሩሳሌም ሀገር በምትገኝ በቤተ መቅደስ በአንድነት ሆነው በጸሎት በመትጋት ቆዩ፡፡ ልጆችዬ መቶ ሃያው ቤተሰብ የሚባሉት 12ቱ ሐዋርያት፣ 72ቱ አርድእት/አገልጋዮች/ እና 36ቱ ቅዱሳን አንስት/ሴቶች/ ናቸው፡፡

ከዕርገት በኋላ በአሥረኛው ቀን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ሐዋርያት ወዳሉበት፣ በጸሎትና በምሥጋና ወደ ሚተጉበት ሥፍራ በእሳት አምሳል /ምሳሌ/ ወርዶ በእያንዳንዳቸው ላይ ተቀመጠባቸው፡፡ ይሄንንም  ሁኔታ ተከትሎ  ምስጢር ተገለጠላቸው፣ ይፈሩ የነበሩት ሐዋርያትም ወንጌልን ለማስተማር ደፋሮች ሆኑ፣ በተለያየ ቋንቋዎች እንዲናገሩ እውቀት ተሰጣቸው፤ የእግዚአብሔርንም ጸጋ ተቀበሉ፡፡ ይህንን ታላቅ ኀይል እና ሰማያዊ ስጦታን የሰጣቸውን እግዚአብሔርን በታላቅ ዝማሬና እልልታ አመሰገኑት፡፡

Saturday, June 15, 2013

ዕርገተ ክርስቶስ


በመ/ር ምሥጢረ ሥላሴ ማናየ
“አልቦ ዘዐርገ ውስተ ሰማይ ዘእንበለ ዘወረደ እምሰማይ ወልደ እጓለመሕያው” ዮሐ.3፥13

Ereget

ከሰማይ ከወረደው የሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም፡፡ እርሱም በሰማይ የሚኖረው ነው፡፡ ይህ ኃይለ ቃል ክብር ምስጋና ይግባውና ስለጌታችን፣ አምላካችን፣ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት መውረድ ከድንግል ማርያም መወለድ እና የሰውነቱን ሥራ ጨርሶ በክብር ወደ ሰማይ ማረጉን የሚገልጽ ነው፡፡ እንደሚታወቀው አምላካችን ስለሁለት አቢይ ጉዳዮች ሰው ሆኗል፡፡
  1. ለቤዛነት /ዓለምን ለማዳን/
  2. ለአርአያነት /ምሳሌነት/
የሰውን ልጅ በመውደዱ ልዑል ባሕርዩን ዝቅ አድርጎ ከሰማይ ወረደ ሥጋ ለበሰ በምድር ላይ ተመላለሰ፤ ምድርን በኪደተ እግሩ ቀደሰ፤ ድውያንን ፈወሰ፤ ፍጹም ሰው እንደ መሆኑ ተራበ ፍጹም አምላክ መሆኑንም ያስረዳ ዘንድ አምስት ገበያ ሕዝብ በአምስት እንጀራ በሁለት ዓሣ አጠገበ ማቴ.14፥19 ለእኛ አርአያና ምሳሌ ለመሆን ዝቅ ብሎ የደቀ መዛሙርቱን እግር አጠበ ዮሐ.13፥14 እኛም ፍለጋውን እንከተል ዘንድ “አንትሙኒ ከመዝ ግበሩ ለቢፅክሙ” እናንተም ለባልንጀሮቻችሁ እንዲሁ አድርጉ ብሎ አዘዘ፡፡ መምሕረ ትሕትና ነውና በዚህ ዓይነት መልኩ ሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር በዚህ ዓለም ኖረ ለሐዋርያት ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ወንጌልን አስተማራቸው ትምህርት በሚገባ ከተረዳለት በኋላ ለድኅነተ ዓለም በማዕከለ ምድር በቀራንዮ ተሰቀለ፡፡