ነገረ ማርያም

ነገረ ማርያም ክፍል፦ ፲፮

«ስለ ጻድቁ ስለ ዮሴፍ የምንናገረውን እንወቅ፤»
          የቊስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳስ የነበረው ቅዱስ ኤራቅሊስ፦ ከቅዱስ ማቴዎስ ወንጌል፥ «የበኲር ልጅዋንም እስከምትወልድ ድረስ አላወቃትም፤» የሚለውን ንባብ በተረጐመበት አንቀጽ ላይ፥ «ናእምር እንከ ዘንሔሊ በእንተ ብፁዓዊ ዮሴፍ ቅዱስ ወምእመን፥ እስመ ውእቱ ኢያእመረ ምሥጢረ ዘይትፌጸም በእግዝእትነ ቅድስት ድንግል ማርያም። የታመነ፥ የከበረ፥ የተመሰገነ ስለሚሆን ስለዮሴፍ የምንናገረውን እንወቅ፥ እርሱ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም የሚፈጸመውን ምሥጢር አላወቀምና፤» ብሏል። ይኸውም፦ ትምህርታቸው በሊቃውንት ደረጃ የሁኑ፥ ነገር ግን ቃሉን ያለ መንገዱ የሚተረጉሙ መናፍቃን በመነሣታቸው ለእነርሱ መልስ ይሆን ዘንድ ነው። «የምንናገረውን እንወቅ፤» ማለቱም «እናስተውል፤» ማለቱ ነው። ምክንያቱም ምን ቢማሩ ባለማስተዋል መጥፋት፥ ማጥፋትም አለና ነው። ሊቃውንት ዕውቀታቸውን በትህትና ካልያዙትና በጸሎት ካልጠበቁት በስተቀር መሰናክል እንደሚሆንባቸው ከጥንት ጀምሮ ከተነሡ መናፍቃን መረዳት ይቻላል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በግሉ በጸሎት ከመትጋት ጋር ምእመናንን፦ «በምስጋና እየተጋችሁ ለጸሎት ፅሙዳን ሁኑ። ስለ እርሱ የታሰርሁለትን የእግዚአብሔርን ምሥጢር እንድንናገር፥ እግዚአብሔር የቃሉን በር ይከፍትልን ዘንድ ለእኛም ደግሞ ጸልዩልን፤ ለምኑልንም፤ ልናገርም እንደሚገባኝ እገልጠው ዘንድ ጸልዩልኝ፤» ይል የነበረው በአገልግሎቱ  ችግር እንዳይፈጠር ነበር። ቈላ ፬፥፪-፬። በመሆኑም ሐዋርያውን አብነት አድርጎ፥ በጸሎት የተጋ፥ በትህትና ያጌጠ፥ በደጋግ ምእመናን ጸሎት የተጠበቀ ቅዱስ ኤራቅሊስ «አላወቃትም፤» የሚለውን እንደሚከተለው ተርጉሞ አስተምሯል። 

 

No comments:

Post a Comment