Tuesday, March 12, 2013

አርባ መአልትና አርባ ሌሊት ጾመ ማቴ.4፥2


በመ/ር ምሥጢረሥላሴ ማናየ
ይህ ከላይ ያነሣነው ርዕስ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችንና አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አርባ መአልትና አርባ ሌሊት መጾሙን ያስተምረናል፡፡
በዚህ ኀይለ ቃል ሁለት ታላላቅ ቁም ነገሮችን ቃላትን እንመለከታለን

  1. አርባ መአልትና አርባ ሌሊት
  2. ጾም የሚሉት ናቸው፡፡

በቅድሚያ አርባ መአልትና አርባ ሌሊት የሚለውን ከእነ ምስጢሩ እንመለከተዋለን፡፡ ቀጥለን ደግሞ ጌታችንስ ለምን አርባ መአልትና አርባ ሌሊት ጾመ? የሚለውን እንመለከታለን እግዚአብሔር አይነልቡናችንን ይክፈትልን፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን የፈጠረውን የሰው ልጆችን አባት አዳምን፣ በልጅነት አክብሮ ገነት ያስገባው በፈጠረው በአርባ ቀኑ ነው፡፡ “ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ እግዚአብሔር ዘገብሮ ለአዳም” አዳምን የፈጠረ እግዚአብሔር ቅዱስ ነው እያሉ እያመሰገኑ መላእክት ወደገነት አስገብተውታል /ቀሌ.4፥/

Saturday, March 9, 2013

የዐቢይ ጾም ስብከት


በአያሌው ዘኢየሱስ

ሐዋርያዊትና ኦርቶዶክሳዊት በሆነችው በቅድስቲቱ ቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ጾም እንደ እንግዳ ደራሽ፤እንደ ወንዝም ፈሳሽ በድንገት የተጀመረ ሥርዓተ አይደለም፡፡ በተለይም በአዲስ ኪዳን ዘመን ጾም ሰው ሠራሽ ሕግ ሳይሆን መድኀኒታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ የመጀመሪያ አድርጎ የሠራው ሕግ ነው፡፡ ጌታ በመዋዕለ ስብከቱ በአንድ ወቅት ከመጥምቁ ዮሐንስና ደቀ መዛሙርት ጾምን አስመልክቶ የቀረበለት ጥያቄና የሰጠው መልስ አለ፡፡ ያቀረቡለት ጥያቄ፡- «. . .  እኛና ፈሪሳውያን ብዙ ጊዜ የምንጦመው፤ ደቀ መዛሙርትህ ግን የማይጦሙት ለምንድር ነው?» (ማቴ 914)  የሚል ነበር፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጣቸው መልስ እንዲህ የሚል ነበር፡- «. . . ሚዜዎች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ ይችላሉን; ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል፤በዚያን ጊዜም ይጦማሉ፡፡» ማቴ 915፡፡ ጌታ በዚህ መልሱ ውስጥ ራሱን  በሙሽራ ደቀ መዛሙርቱንም በሚዜዎች በመመሰል እርሱ በመንፈስ ሳይሆን በሥጋ ከእነርሱ በዕርገቱ ተለይቶ ከመሔዱ በፊት ሊያዝኑ፣ ሊተክዙና ከመባልዕት ሊከለከሉ እንደማይችሉ ነገር ግን በዕርገቱ ሲለያቸው መጾም እንደሚጀምሩ ተናገረ፤አስተማረ፡፡ በመሆኑም «በዚያን ጊዜም ይጦማሉ፡፡» የሚለው ሐረግ እርሱ በገዳመ ቆሮንቶስ የጣለውን የጾም መሠረት እነርሱ ከዕርገቱ በኋላ አጠናክረው እንደሚቀጥሉበት የሚያጎላ ነው፡፡