በቤካ ፋንታ
- እግዚአብሔር የሠራት ቀን ይህች ናት/ መዝ 118፥24/
ይህች ታላቅ ዕለት ከቅድስት ሥላሴ አንዱ አካል የሆነው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ለቅዱሳን ሐዋርያት፣ ለቅዱሳን አርድእትና ለቅዱሳት ሴቶች የተገለጠባት ዕለት ናት፡፡ እነዚህ ሁሉ በጸሎት ተግተው በሚጸልዩበት ወራት መንፈስ ቅዱስ በተከፋፈሉ የእሳት ልሳን አምሳል የወረደበት ቅዱስ ቀን ነው፡፡
አስቀድሞ ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱሳን ሐዋርያት ደብረ ዘይት በተባለ ታላቅ ተራራ ላይ ሳሉ እንዲህ ብሎ አስተምሯቸው ነበር “ኀይልን ከላይ ከአርያም እስክልክላችሁ ድረስ በኢየሩሳሌም በጸሎት ቆዩ፡፡”/ሉቃ 24፡36/ መቶ ሃያው ቤተሰብም በኢየሩሳሌም ሀገር በምትገኝ በቤተ መቅደስ በአንድነት ሆነው በጸሎት በመትጋት ቆዩ፡፡ ልጆችዬ መቶ ሃያው ቤተሰብ የሚባሉት 12ቱ ሐዋርያት፣ 72ቱ አርድእት/አገልጋዮች/ እና 36ቱ ቅዱሳን አንስት/ሴቶች/ ናቸው፡፡
ከዕርገት በኋላ በአሥረኛው ቀን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ሐዋርያት ወዳሉበት፣ በጸሎትና በምሥጋና ወደ ሚተጉበት ሥፍራ በእሳት አምሳል /ምሳሌ/ ወርዶ በእያንዳንዳቸው ላይ ተቀመጠባቸው፡፡ ይሄንንም ሁኔታ ተከትሎ ምስጢር ተገለጠላቸው፣ ይፈሩ የነበሩት ሐዋርያትም ወንጌልን ለማስተማር ደፋሮች ሆኑ፣ በተለያየ ቋንቋዎች እንዲናገሩ እውቀት ተሰጣቸው፤ የእግዚአብሔርንም ጸጋ ተቀበሉ፡፡ ይህንን ታላቅ ኀይል እና ሰማያዊ ስጦታን የሰጣቸውን እግዚአብሔርን በታላቅ ዝማሬና እልልታ አመሰገኑት፡፡