IN THE NAME OF
THE FATHER AND THE SON AND THE HOLY SPIRIT, ONE GOD. AMEN.
''Filseta''
is a pre-assumption fast instituted by the apostles. It lasts for
15days and is commonly refferd as ''little lent''. It is a sober and earnest time in which people of all age participate. Even small children
under seven years of age, the sick, and the sojourner, who are normally exempt from the discipline, maintain the fast of the assumption. Apostles continued to be sad and
sorrowful, because of her separation from them, and because they were
left orphans by her; for Our Lord had given them the hope that they
would see her in the flesh. The Ethiopian book of saints-the synaxarium /January 29/ discusses the assumption. Filseta is the time when the faithful examine their lives in light of the purity, holiness, and obedience of the Virgin. In this spirit one fasts,one prays,one dedicates anew his or her life to God.
“ተንሥእ እግዚኦ ውስተ ዕረፍትከ አንተ ወታቦተ መቅደስከ፤ አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፥ አንተና የመቅደስህ ታቦት” /መዝ.131፥8/
“ተንሥኢ ወንዒ ቅርብትየ እንቲአየ ሠናይት ርግብየ ውስተ ጽላሎተ ኰኲሕ ቅሩበ ጥቅም፡፡ አቅራቢያዬ መልካሟ ርግብየ ተነሽ፤ ነዪ፤ በግንቡ አጠገብ ወዳለው ወደ ዋሻው ጥላ፡፡” /መኃ.2፥10-14/
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እመቤታችንን መቅደሱ፥ ታቦቱ፣ ማደሪያው፣ መንበሩ እናቱ አድርጎ መረጣት፡፡
ስለዚህ ምክንያት አብ ጠበቃት ወልድ በተለየ አካሉ ሥጋን ከርሷ ተዋሐደ መንፈስ ቅዱስ አጸናት፡፡ እመቤታችን በዚህ
ኃላፊ ዓለም ለ64 ዓመት ቆይታለች፡፡ ጥር ሰኞ ይብታል ሰኞ እስከ ሰኞ 8 ሰኞ እስከ ሰኞ 15፣ ሰኞ እስከ ሰኞ
22፣ ሰኞን ትቶ እሑድ ጥር 21 ቀን እመቤታችን አርፋለች፡፡ ሐዋርያት ባጎበር አድርገው ወደ ጌቴ ሴማኒ ይዘዋት
ሲሄዱ አይሁድ “ቀድሞ ልጇን ሰቅለን ብንገድለው ደቀ መዛሙርቱ ተነሣ፣ ዐረገ” እያሉ ሲያውኩን ኖሩ፤ ዛሬ ደግሞ
እርሷን ተነሣች፣ ዐረገች እያሉ ሊያውኩን አይደለምን? በእሳት እናቃጥላታለን” ብለው ተነሡ፡፡ ታውፋንያ የሚባል
አይሁዳዊ ተራምዶ አጎበሩን ጨበጠው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል የታውፋንያን ሁለት እጁን በሰይፍ መትቶ ቀጣው፡፡
በዚህም የታውፋንያ ሁለት እጁ ከአጎበሩ ተንጠልጥሎ ቀረ፡፡ ከዚያ በኋላ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌላዊውን
ቅዱስ ዮሐንስ ጨምሮ በደመና ነጥቆ ከገነት በዕፀ ሕይወት ሥር አኖራት፡፡
ሐዋርያት ዮሐንስን “እንደምን ሆነች” አሉት፡፡ እርሱም፡- “በገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር አለች” አላቸው፡፡ “ዮሐንስ
አይቶ እኛ ሳናይ” ብለው፤ በነሐሴ መባቻ ጾም ጀመሩ፤ ሰኞ ነሐሴ 1 ቀን ጀምረው እሑድ ነሐሴ 14 ቀን
ፈጽመዋል፡፡ በዚሁ ቀን ጌታችን ትኩስ በድን አድርጎ የእመቤታችንን ሥጋ ሰጥቷቸው ቀብረዋታል፡፡ እርሷም እንደ ልጇ
በተቀበረች በሦስተኛው ቀን /ማክሰኞ/ ተነሥታ አርጋለች፡፡ “ከመ ትንሣኤ ወልዳ” ያሰኘውም ይህ ነው፡፡ በዚሁ ጊዜ
ከሐዋርያት ወገን የሆነው ቅዱስ ቶማስ አልነበረም፡፡ ደመና ጠቅሶ ከሀገረ ስብከቱ /ከሕንድ/ ሲመጣ ስታርግ
አገኛት፡፡ “ወፈቀደ ይደቅ እምደመናሁ” ይላል፤ ተበሳጨ፡፡ “ቀድሞ የልጅሽን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁ፤ ዛሬ ደግሞ
ያንቺን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁኝ” አለ፡፡ በዚህ ጊዜ የልቡናን ሐዘን የምታቀል እመቤታችን፡- አይዞህ አትዘን እኒያ
ትንሣኤዬን ዕርገቴን አላዩም፡፡ አንተ አይተሃል፡፡ ተነሣች፣ ዐረገች ብለህ ንገራቸው፡፡” ብላ የያዘችውን ሰበን
ሰጥታ ሰደደችው፡፡ ከዚህ በኋላ ሄዶ፤ “የእመቤታችን ነገር እንደምን ሆነ?” አላቸው “ሥጋዋን አግኝተን ቀበርናት”
አሉት፡፡ እርሱም “ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር ተዉ ይህ ነገር አይመስለኝም” አላቸው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ “አንተ እንጂ
ልማድህ ነው፡፡ አንተ ብቻ ተጠራጥረህ አትቀርም፤ አንተ እየተጠራጠርህ ሰውን ሁሉ ስታጠራጥር ትኖራለህ” አለው፡፡
እርሱም የያዘውን ያውቃልና ጸጥ ብሎ ይሰማቸዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ቅዱስ ጴጥሮስ ተቆጥቶ ሂዶ መቃብሩን ቢከፍተው
የእመቤታችን ሥጋዋን አጥቷል፡፡ በዚህም ምክንያት ደንግጦ ቆመ፡፡ ይህን ጊዜ ቅዱስ ቶማስ “አታምኑኝም ብዬ ነው
እንጂ እመቤታችንስ ተነሣች ዐረገች” አላቸው፡፡ የያዘውንም ሰበን እያሳያቸው፡- “ቅዱስ ሥጋዋን የገነዛችሁበት ጨርቅ
/ሰበን/ ይህ አይደለምን” ብሎ ሰበኑን ሰጣቸው፡፡ ይህንንም ለበረከት ተካፍለውታል፡፡ ከዚህ በኋላ በዓመቱ “ቶማስ
ትንሣኤሽን ዕርገትሽን አይቶ እኛ ሳናይ በማለት ጾም ጀመሩ፡፡ በ16ኛው ቀን እመቤታችንን መንበር ቅዱስ ጴጥሮስን
ንፍቅ ቄስ፣ እስጢፋኖስን ሠራዒ ዲያቆን አድርጎ ራሱ ቀድሶ አቁርቦአቸዋል፡፡
ስለዚህ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከጌታችን በኋላ ከክርስቲያኖች ሁሉ በፊት የትንሣኤንና የዕርገትን ክብር
አግኝታ ልዑል እግዚአብሔር ባዘጋጀላት ልዩ ሕይወት እንደምትኖር ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች፡፡ ምእመናን ሁላቸውም በየጾታቸውና በየመአረጋቸው ቀን በቅዳሴ፣ ሌሊት በሰዓታት በማኅሌት በኪዳን ቃለ እግዚአብሔርን በመስማትና ስብሐተ እግዚአብሔርን በማድረስ ይወሰናሉ፡፡
በእነዚህ አሥራ አምስት ቀናት የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ ውዳሴዋና ቅዳሴዋ ተራ በተራ ይተረጎማሉ፡፡ ምእመናንም በፍቅርና በሃይማኖት የሚሰጠውን ትምህርት ይሰማሉ፡፡ ሶሪያዊው ቅዱስ ኤፍሬም እመቤታችንን ባመሰገነበት በውዳሴ ማርያም ድርሰቱ ከተናገራቸው ኀይለ ቃላት፡- “ነጸረ አብ
እምሰማይ፡፡ ወኢረከበ ዘከማኪ፡፡ ፈነወ ዋሕዶ ወተሰብአ እምኔኪ፡፡ ማለትም እግዚአብሔር አብ በሰማይ ሆኖ አየ፤
አየና እንዳች ያለ ባያገኝ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለውን ልጁን ወዳንቺ ላከው፡፡ ካንቺም ከሥጋሽ ሥጋ ከነፍስሽ ነፍስ
ነሥቶ ሰው ሆነ፡፡” በማለት ያመሰገነበት ቃል ይገኛል፡፡ /ውዳሴ ማርያም ዘረቡዕ/ ይህ ቃል እመቤታችን ከፍጥረታት
ሁሉ የከበረች በንጽሕናዋና በቅድስናዋ የተነሣ አምላክ ከእርሷ ተወልዶ /ሰው ሆኖ/ ዓለምን እንዲያድን ምክንያት
የሆነችበትን ያስረዳል፡፡ በዳዊት መዝሙር ሰፍሮ በምናገኘው ቃል እግዚአብሔር አምላካችን የሚያስተውል እርሱንም
የሚፈልግ ልብ ከሰዎች ልጆች እንዲያገኝ ቢመለከት አንዳች እንኳ እንዳጣና ሁሉ እንዳመፁ ተጠቅሶአል፡፡
/መዝ.13፥2-3/ ስለሆነም ነው ይህንኑ ቃል አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው፡- “በአማን ነጸረ እግዚአብሔር አብ እምሰማይ
ምሥራቀ ወምዕራበ ሰሜነ ወደቡበ፡፡ አስተንፈሰ ወአጼነወ፡፡ ወኢረከበ ዘከማኪ፡፡ ወሠምረ መዓዛ ዚአኪ፡፡ ማለትም
እግዚአብሔር በልዕልና ሆኖ አራቱን ማዕዘን በእውነት ተመለከተ አስተናፈሰ አሸተተ ነገር ግን በንጽሕና በቅድስና
የተዘጋጀች እንዳንቺ ያለች አላገኘም፡፡ መዓዛ ንጽሕናሽን መዓዛ ቅድስናሽን ወድዶ ለተዋሕዶ መረጠሽ፡፡” በማለት
የተረጎመው፡፡
የተወደዳችሁ ምእመናን ለበረከት ይሆነን ዘንድ ከአባቶቻችን ቅዱሳን ሊቃውንት መካከል አንዱ የሆነው ቅዱስ ኤፍሬም
ሶሪያዊ እመቤታችንን ካመሰገነበት የምስጋና ድርሰቱ አንዱን አንቀጽ እናንሣና ለአሁኑ እንሰነባበት፡፡ “ተፈሥሒ ኦ ወላዲተ እግዚእ ሐሤቶሙ ለመላእክት፡፡” የሚለው ቃል በቅዱስ ኤፍሬም የምስጋና ድርሰት ይገኛል፡፡
/የማክሰኞ ውዳሴ ማርያም/ ይህንን የምስጋና ድርሰት አባቶቻችን መምህራን እንዲህ ተርጉመውታል፡፡ “የመላእክት
ደስታቸው የሚሆን ጌታን የወለድሽው ተፈሥሒ ደስ ይበልሽ፡፡ ለሊሁ ዓለሞሙ፣ ወለሊሁ ተድላሆሙ፣ ወለሊሁ ሀገሮሙ
እንዲል፡፡ አንድም ሥጋዌውን ተልከው ለነቢያት የሚነግሩ መላእክት ናቸው፡፡ ከዚህ የተነሣ በአጭር ቁመት በጸባብ
ደረት ተወስኖ አይተውት፤ ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ብለው አመስግነውት፤ በጣዕም ላይ ጣዕም
በጸጋ ላይ ጸጋ ተጨምሮላቸው ደስ ብሏቸዋልና፡፡ አንድም የመላእክት ደስታቸው የምትሆኝ ጌታን የወለድሽው ተፈሥሒ ደስ
ይበልሽ፡፡ ንጽሕናዋን ቅድስናዋን እያዩ ደስ ይላቸዋልና ሐሤቶሙ ለመላእክት አለ፡፡” እንግዲህ ቅዱስ አባ ሕርያቆስ፡- “ኦ አንትሙ ሕዝበ ክርስቲያን ወበከመ ሰማዕክሙ ዘንተ ቃለ ቅዳሴሃ ለማርያም ከማሁ
ያስምዕክሙ ቃለ መሰናቁት ዘሕፃናት” እንዳለው፤ ይህንን የእመቤታችንን ምስጋና ውዳሴ ለመስማት ለማንበብ ያበቃን
ፈጣሪያችን በቸርነቱ ብዛት ከጣዕሙ ብዛት አጥንትን የሚያለመልም የመላእክትን ምስጋና የሕይወትን ቃል ያሰማን፡፡
ከእመቤታችን ከወላዲተ አምላክ ከድንግል ማርያም በረከት ረድኤት ያሳትፈን፡፡ ፍቅሯን በልባችን፣ ጣዕሟን በአንደበታችን ይሳልልን ያሳድርብን አሜን፡፡
No comments:
Post a Comment