ክርስቲያኖች ከእግዚአብሔር በጸጋ እንደተወለዱ በማመን
ለእግዚአብሔር ያላቸውን ፍቅር ከሚገልጡባቸው ነገሮች አንዱ ጾም ነው፡፡ ጾም ፍቅረ መብዓ ከመሆኑ በተጨማሪ ታዛዥነትንና
የገቡትን ቃል ኪዳን ጠባቂነትንም ማሳያ ነው፡፡ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር አርአያ ተፈጥሯአል፡፡ ኃጢአት ሠርቶ የእግዚአብሔር
አርአያነቱን ቢያጠፋውም እግዚአብሔር ግን በአርአያው ሲፈጥረው ምን ያህል እንደሚወደው ማረጋገጫ ስለነበር በኃጢአት ሲወድቅም
እንደወጣ ይቅር ሳይል ሊፈልገው መጣ፡፡ እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ሊፈልግ የመምጣቱ ተስፋ የተነገረበትንና ሱባኤ የተቆጠረበትን
ዕለት ለማየት በመናፈቅ ከቀረበው መሥዋዕት አንዱ ጾም ነበር፡፡
ሰው በኃጢአት ቢወድቅም ፈጣሪው ሊያነሳው፤ ቢጠፋ ሊፈልገው
እንደሚመጣ በተስፋ ሲጠብቀው ወልደ አምላክ ሰው መሆኑ የተረጋገጠ እውነት ነው፡፡ ስለዚህ አዳም የልደቱን ነገር በትንቢት
መነፅርነት ሲመለከተው /በነቢያቱ ትምህርትና ስብከት/፣ በሚኖርበት ዓመተ ፍዳ የምሥጢረ ሥጋዌ ብርሃን ከሩቅ
ሲመለከተው ኖረ፡፡ ምሥጢረ ሥጋዌን በትንቢት መነፅርነት ማየቱም መከራውን እንዲቋቋመው የተስፋ ስንቅ ሆነው፡፡