Monday, February 25, 2013

ፍርድ ለነነዌ÷ ሥልጣን ለነነዌ




በዲ/ን ዮሴፍ ይኩኖአምላክ

ኮናኔ በርትዕ÷ ፈታሄ በጽድቅ÷ የሆነው መድኀኒዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ጻፍት ፈሪሳውያንን በቋንቋቸው በዕብራያስጥ ቢያስተምራቸው “እንደ ሙሴ፡- ባሕር ከፍለህ÷ ጠላት ገድለህ÷ ደመና ጋርደህ÷ መና አውርደህ፣ እንደ ኢያሱ፡- በረድ አዝንመህ÷ ፀሐይ አቁመህ÷ እንደ ጌዴዎን፡- ፀምር ዘርግተህ ጠል አውርደህ፣ እንደ ኤልያስ ሰማይ ለጉመህ እሳት አዝንመህ ልታሳየን እንወዳለን” የሚል ጥያቄ በቀረበለት ጊዜ የሰጣቸው ምላሽ “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል÷ ከነቢዩ ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት  አይሰጠውም፡፡ ዮናስ በዓሣ አንበሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ÷ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል፡፡ የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈረዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና÷ እነሆም ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ” የሚል ነው፡፡ ጻፍት ፈሪሳውያንን ምልክት ያስፈለጋቸው ዋነኛ ምክንያት በጌታችንና በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት ለማመን አልነበረም፤ ይልቅስ እንደ ዘማ ሴት ምልክት በምልክት እየተደራረበ ማየትን በመናፈቅ ነው፡፡

Friday, February 15, 2013

የየካቲት ኪዳነ ምህረት ዓመታዊ ክብረ በዓል

                                      በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! 

በሀገረ ቤልጅየምና በዙሪያዋ ለምትኖሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምእመናን በሙሉ፤  

 በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በእናታችን በወላዲተ አምላክ ቅድስት ድንግል ማርያም ስም መንፈሳዊ  ሰላምታችንን እያስቀደምን: እንኳን ለእናታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ ክብረ በዓል በሠላም አደረሳችሁ። የየካቲት ኪዳነ ምህረትን በዓል በዕለቱ የካቲት 16፣ 2005ዓ.ም (Feb 23, 2013) ከዋዜማው (የካቲት15, Feb.23) ጀምሮ; ከየአጥቢያ ቤተክርስቲያን በሚመጡ አባቶች እና ምእመናን በሚገኙበት ሌሊት በማኅሌት እና  ጠዋት በቅዳሴ በደመቀ ሁኔታ ይከበራል። ቤተክርስትያኗ ከዋዜማው ምሽት 22፡00 ሰዓት ጀምሮ ክፍት ስለምትሆን በሰዓቱ ተገኝተው ከልዩ ልዩ የአዳር መርሐ ግብሮች ተካፋይ እንዲሆኑና ሌሎችንም እንዲጋብዙ ቅድስትቤተ-ክርስቲያን ጥሪዋን ታስተላልፋለች።  ሕንፃ ቤተ-ክርስትያኑ ከእኩለ ቀን (11፡30) በሗላ ለሌላ አገልግሎት ስለሚፈለግ በሰዓቱ ቀደም ብለው በመገኘት የበረከቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ በትህትና እንጋብዛለን።   ይህ መልዕክት የማይደርሳቸውን ምዕመናንንም በመቀስቀስ የበረከቱ ተሳታፊ እናድርጋቸው።             

 የአምላካችን ረድኤት የቅድስት ኪዳነ ምሕረት አማላጅነት ከሁላችን ጋር ይሁን።

Tuesday, February 5, 2013

“የዲያብሎስን ሥራ ይሽር ዘንድ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ፡፡” 1ኛ ዮሐን.3፥8




ምንጭ :ከማህበረ ቅዱን ድህረ ገፅ የተወሰደ
በዲ/ን ኃይለ ኢየሱስ ቢያ
ይህንን ኀይለ ቃል የተናገረው  ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ነው፡፡ የተናገረበት ምክንያት፡-
የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ የጌታችን መድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ /ሰው ሆኖ የማዳን ሥራውን/ መፈጸሙን ለመግለጥ  የተናገረው /የጻፈው ኀይለ ቃል ነው፡፡
  • መገለጥ ማለት ፡- ረቂቁ አምላክ በተአቅቦ ርቀቱን ሣይለቅ ውሱን ሥጋን ውሱኑም ሥጋ በተአቅቦ ውስንነቱን ሳይለቅ ረቂቅ መለኮትን የሆነበት በአጭር ቃል የቃል ግብር ለሥጋ የሥጋ ግብር ለቃል የሆነበት ረቂቅ ምስጢር ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ቀዳማዊ ደኃራዊ የሆነው አምላክ ሞት የሚስማማው ሆነ፤ ዘመን የሚቆጠርለት ሥጋ ዘመን የማይቆጠርለት ሆነ፡፡ ሥጋ በማይመረመር ምስጢር የመለኮትን ገንዘብ ገንዘቡ ቢያደርግ “ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ ሞቼም ነበርሁ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ” /ራእ.1፥17/ ማለት የቻለበት ምስጢር ነው፡፡ የረቀቀው ገዝፎ የገዘፈው ረቆ፣ ሰማያዊው ምድራዊ  ምድራዊው ሰማያዊ ሆኖ መታየት ማለት ነው፣  ከዓለም ተሰውሮ የነበረው ምስጢር  ግልጥ ሆኖ መታየት ማለት ነው ይህንንም ምሥጢር ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በጢሞቴዎስ  መልእክቱ “እግዚአብሔርን የመምሰል ምስጢር ያለጥርጥር ታላቅ ነው፤ በሥጋ የጠገለጠ፣ በመንፈስ የጸደቀ፣ ለመላእክት የታየ፣ በአሕዛብ የተሰበከ፣ በዓለም የታመነ፣ በክብር ያረገ /1ጢሞ 3፥16/ በማለት፡፡ ከልደት እስከ ዓቢይ ጾም መጀመሪያ  ያለው ጊዜ  ዘመነ አስተርእዮ /የመገለጥ ዘመን/ የመታየት ወቅት ይባላል::

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ በፍጹም ተዋሕዶ ሰው መሆኑን /ዓለምን ለማዳን መወለዱን የምንገልጽበት ወቅት ነው፡፡

የእግዚአብሔር መገለጥም በ3 ዘመናት ከፍሎ ማየት ይቻላል

Thursday, January 17, 2013

ጥምቀት


በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ


በሰው ልጅ ዘላለማዊ ድኅነት ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው ሥርዓተ ጥምቀት ከሌሎቹ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን በቀዳሚነት የሚፈጸምና የማይደገም ሥርዓት ነው፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “አንዲት ጥመቀት” በማለት የሥርዓተ ጥምቀትን አለመደገምና አለመሠለስ ገልጦ ተናግሯል /ኤፌ.4፥5/፡፡ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ተመዝግቦ እንደሚገኘውና፥ የታናሽ እስያ ክፍል በሆነችው ቁስጥንጥንያ በ381 ዓ.ም. የተሰበሰቡ 150 የሃይማኖት አባቶቻችን “ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት ለሥርየተ ኀጢአት፣ ለኀጢአት ማስተሥረያ /ኀጢአትን በምታስተሠርይ/ በአንዲት ጥምቀት እናምናለን” በማለት የጥምቀትን አንድ መሆንና ኀጢአትን በደልን የምታርቅ፣ የምታስወግድ ስለመሆኗ በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ተመርተው ተናግረዋል፡፡ ሃይማኖታቸውንም ገልጠዋል፡፡

Friday, January 11, 2013

ጥበብ ዘየዓቢ እምነ ኩሉ ጥበብ ከጥበብ ሁሉ የሚበልጥ ጥበብ

ጥር 1 ቀን 2005 ዓ.ም. 
በዲ/ን እሱባለው

christmas 1
ከሰማይ በታች ባሉት ፍጥረታት ላይ በገዢነት የተሾመው የዕለተ ዓርብ ፍጥረት የሰው ልጅ በምክረ ከይሲ ተታልሎ ከፈቃደ እግዚአብሔር ፈቀቅ በማለቱ ሞትን ወደ ዓለም አስገብቷል፡፡ በዚህም የተሰጠውን ነጻነት በገዛ ፈቃዱ አሳልፎ ሰጠ በምትኩም ወደ ሰይጣን ምርኮኝነት እና ጽኑ አገዛዙ ፈጽሞ ሄደ፡፡

መፍቀሬ ሰብእ አምላካችንም እንደ ወጣን እንቀር ዘንድ ተቅበዝባዦች እንድንሆንም አልወደደም፤ ባማረ በተወደደ ቸርነቱ ጎበኘን እንጂ፡፡ ወኢኃደጎሙ ውስተ ኃጕል ለዝሉፉ በዕደ ሰይጣን - በሰይጣን እጅ እንደተያዙ ሊቀሩ  በጥፋት ውስጥ አልተዋቸውም እንዲል፡፡ ከነበርንበት ጉስቁልና ያድነን ዘንድ የሰይጣን ምክሩን ያፈረሰው በአምላክነቱ፣ በከሃሊነቱ፣ ከጌትነቱ ወገን በምንም በምን ድል አልነሣውም ወኢሞኦ በኃይሉ መዋኢት ወኢኃየሎ በክሂሎቱ ወኢበምንትኒ እምዕበዩ አላ በትሕትናሁ ወፍትሐ ጽድቁ በትሩፋተ ምሥጢር እንግዳ- እንግዳ በሚሆን ተዋርዶ(ትሕትና) በሠራው ሥራ ድል ነሣው እንጂ፡፡


Sunday, November 25, 2012

ሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ







          ......«ሐምሌ 22 ቀን 1928  ስምንት ወታደሮች በስተጀርባቸው ሃያ እርምጃ ርቀው ተንበርክከው በተንጠቀቅ ቆሙ። ወዲያው አዛዡ «ተኩስ» በማለት ትእዛዝ ሲሰጥ ስምንቱም ተኩሰው መቷቸው። ግን በስምንት ጥይት ሳይሞቱ ቀሩ። መሞታቸውንና አለመሞታቸውን ለማረጋገጥ ዶክተር ተጠራ። ዶክተሩም እንዳልሞቱ አረጋገጠ። ከዚያም ሌላ ወታደር በሦስት የሽጉጥ ጥይት ራስ ቅላቸውን መትቶ ገደላቸው። .........

በ1875 ዓ.ም. በሰሜን ሸዋ አገረ ስብከት ሰላሌ አውራጃ ፍቼ ከተማ ተወለዱ። ወላጆቻቸው ዕድሜያቸው ገና በወግ ለትምህርት ሳይደርስ ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም በመውሰድ ባሕታዊ ተድላ ለተባሉ መምህር አደራ ሰጧቸው። በዚያው ገዳም የንባብ ቤቱንና የዜማውን የትምህርት ደረጃዎች በሚያስገርም ሁኔታ በአጭር ጊዜ አቀላጥፈው በመጨረስ ገና በልጅነት የዕድሜ ደረጃቸው ሦስተኛውን የቅኔ ትምህርት ጀምረው በአጭር ጊዜ ሙሉ ቤት ተቀኙ። ይህንኑ የቅኔ ትምህርት ለማስፋፋት በምዕራብ ጎጃም አገረ ስብከት ወደሚገኘው የቅኔ ትምህርት ማዕከል ዋሸራ ተሻግረው ለመምህርነት የሚያበቃውን ትምህርት ፈጽመው አስመሰከሩ።