Sunday, September 7, 2014

ለውጥ በሌለው ሕይወት አቆጣጠር - ዛሬ ስንት ዓመተ ምሕረት ነው ?



Dn Melaku ezezew
አንድ ሶርያዊ ክርስቲያን የሚከተለውን ደብዳቤ 1983 . ጽፎ ነበር፡፡ ደብዳቤው እንዲህ ይነበባል፡-
«እስከ 1970 . (የተወለደው 1943 . ነው) «በቤተ ክርስቲያን ትምህርት መሠረት ሥጋ ወደሙ እቀበል ነበር፣ አሥራት አወጣ ነበር፣ ገዳማትን ለመርዳት የተቋቋመ ማኅበር አባል ሆኜ ሌት ተቀን እሠራ ነበር፣ ሁል ጊዜ በመንፈሳዊ ሕይወቴ ውስጥ የመለወጥ ስሜት ነበረኝ፣ ለመማር፣ ለመጾምና ለመጸለይ የነበረኝን ትጋት አስታውሰዋለሁ፡፡ ይሁን እንጂ 1970 . መንፈሳዊ ሕይወቴ ባለበት ቆመ፡፡ እንኳን ከበፊት የተሻለ ምግባር ልፈጽም የነበረኝንም እየተውኩት መጣሁ፡፡ ድካምና መሰልቸት ሕይወቴን ተጫጫነው፡፡ ራዕይ አጣሁ፡፡ ከፊት ለፊቴ ምንም ነገር አይታየኝም፡፡ ግድግዳ ያለ ይመስለኛል፡፡ ቤተክርስቲያን በበለጠ ለማገልገል የነበረኝ ጉጉት ሁሉ ሞተ፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በማንኛውም ደብዳቤ ዓመተ ምሕረቱን 1970 እያልኩ እጽፋለሁ፡፡ እስከ አሁን ድረስ (1983 . ማለቴ ነው) በኔ አቆጣጠር 1970 . ነው፡፡ ምክንያቱም ከዚያ በኋላ በኑሮዬ ውስጥ ምንም የተለወጠ፣ ያደገ ወይም የተስተካከለ ነገር የለምና፡፡ ብፁዕ አባታችን፡- እባክዎ ምክርዎን በመለገስ ወደ 1971 . ያሸጋግሩኝ

ሕይወት ካልተለወጠ፣ ካላደገ፣ ሃይማኖት ካልሰፋ፣ ምግባር ካልጸና ትናንት ያሸነፉንን ኃጢአቶች ዛሬ ካላሸነፍን፣ የደከመውን አበርትተን፣ የተሰበረውንካልጠገንን፣ ዘመን ተለውጦ ዘመን ቢተካም፣ የምድርን ዕድሜ እንቆጥራለንን እንጂ እኛ እንደሆንን እንደቆምን ነን፡፡ አንዳንዶቻችን ያኔ ሕጻን ሆነን ሥጋ ወደሙ እንደተቀበልን፣ ሌሎቻችንበወጣትነት ለሰንበት /ቤትና ለጽዋ መርሐ ግብር በነበረን ትጋት ላይ ሌሎችም በማስተማር፣ ቤተክርስቲያንን በማሰራት፣በማስቀደስ በመጸለይና በመጾም፣ በነበረን የጥንት ምግባር አንዳንዶችም ወደ ምንኩስና (ምናኔ) ሲገቡ በነበራቸው የወጣኒነትትጋት እዚያው ላይ ዓመተ ምሕረታችን ቆሟል፡፡

አዲስ አበባ አራት ኪሎ መሐል የአርበኞች ኃውልት አለ፡፡ እዚያ ኃውልት ጫፍ ላይ ሰዓት ተሰቅሏል፡፡ ሰዓቱ የሚያመለክተው አርበኞች አዲስ አበባ የገቡበትን ሰዓት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ቆሟል፡፡ የዛሬው ትውልድ ያንን ሰዓት ሲያየው ጀግኖች አባቶቹ ጠላትን ድል አድርገው ሀገሪቱን ነጻ ያወጡበትን ጊዜ ያስብበታል፡፡ ሰዓት የጥንቲቱን ተግባር ብቻ እያመለከተ ቆሟል፡፡ የዛሬውን ትውልድ ጀግንነትና ዝና የሚያሳይ ሰዓት ግን የለም፡፡ የብዙዎቻችን ሰዓት ቆሟል፡፡ በአንድ ወቅት የሠራነውን መልካም ስራ፣ የነበረን መንፈሳዊ ትጋት፣ የሃይማኖት ጥንካሬና ሰማይ ጥግ የደረሰ ዝና እያመለከተ ቆሟል፡፡ ዛሬ በአቡሻህር አቆጣጠር 2007 . ነው:: በእኛ አቆጣጠርስ ስንት ነው; ሶርያዊ ክርስቲያን «በኔ አቆጣጠር 1970 . ነው» ብሏል፡፡ እርሱ የነበረበትን ዘመን ግን እስከ 1983 . ነበር፡፡


የዘመን መለወጫን በዓል አከበርነውም አላከበርነውም ዘመኑ መለወጡ አይቀሬ ነው፡፡ እያንዳንዷን ቀን ተጠቀምንም አልተጠቀምንም ጊዜው መሮጡ አይቀርም፡፡ እርሱ የራሱን ጊዜ ይቆጥራል፡፡ ይለወጣል፡፡ እኛስ; እስቲ ጊዜ ሰጥተን ራሳችንን እንመርምረው፡፡ በሃይማኖት እየጸኑ፣ በምግባር እየበረቱ፣ በትጋት እየጨመሩ፣ በመንፈሳዊ እውቀት እያበሩ፣ ሰማዕትነትን ይበልጥ እያፈኩ ካልሄዱ ዘመኑ ብቻውን ቢቀየር «እንኳን አደረሳችሁ».ያስብላልን; የአክሱምንም አደባባይ የጎበኘ ሰው ሦስት ነገሮችን መታዘብ ይችላል፡፡ ተጠርቦ ተቀርጾ ሃውልት የሆነ ድንጋይ አለ፡፡ ሃውልት ለመሆን ተጠርቦ ቅርጽ ሳይወጣለት ልሙጥ ሆኖ የቀረ አለ፡፡ ለሀውልትነት ተመርጦ ሳይጠረብ ሳይቀረጽ የቀረ አለ፡፡ በመንፈሳዊ ጉዞም እነዚህ ሦስቱ ነገሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ፡፡ ለሰማያዊ ዋጋ ተመርጠው በብዙ ፈተና ተጠርበውና ተቀርጸው ጉዞአቸውን የፈጸሙ አሉ፡፡ ተመርጠው ተጠርበው ግን ገና ቅርጽ መያዝ ሲቀራቸው ባሉበት የቀሩ አሉ፡፡ በሌላ በኩል ተመርጠው ከመጡ በኋላ ከዚያ ያለፈ ተግባር ላይ ያልዋሉም አሉ፡፡ የእነዚህ የሦስቱም የዘመን አቆጣጠራቸው ይለያያል፡፡ አንዱ በደረሰበት . ሌሎቹ አልደረሱምና፡፡

በወንጌል ታሪኩ የተጠቀሰው የጠፋው ልጅ አባት ልጁ ከጠፋበት ሀገር ሲመለስ «ይህ ልጄ ሞቶ ነበር ህያው ሆኗል».ብሎ ነበር የተናገረው፡፡ ልጅ እኮ ይንቀሳቀሳል፣ ይበላል፣ ይጠጣል ግን ሞቷል ተባለ ለምን; የሱ የዘመን አቆጣጠር ከአባቱ ቤት ሲጠፋ መቁጠሩን አቁሞ ነበርና፡፡ በመንፈሳዊ ጉዞ የነበረው ለውጥ ስላቆመ ሞተ ተባለ፡፡ ትልቁ ጥያቄ ማን ተለወጠ ነው፡፡ ዘመን ተለወጠ; ሰው ተለወጠ; ወይስ ሁለቱም ተለወጡ; ዘመን ይለወጣል፡፡ አይቀሬ ነው፡፡ የስነ ፍጥረት ስርዓት ሁሉ የእግዚአብሔርን ህግ ሳያፋልስ ይኖራልና፡፡ አስቸጋሪው ነገር እርሱ አይደለም፡፡ እስከ ዘመነ ምጽዓት ዘመን ይመጣል፣ ያልፋል፣ በሌላ ይተካል፡፡ ሰው ተለወጠ; ለሚለው ጥያቄ መልስ ማግኘት ግን ከባድ ነው፡፡ ይህን ጥያቄ ከባድ ያደረገው በሰው ኑሮ ውስጥ ሦስት ዓይነት ለውጥ ስላለ ነው፡፡ በመንፈስ መለወጥ፣


በአካል መለወጥ፣ በባሕላዊም ይሁን በዘመናዊ መንገድ በሚገኝ እውቀት የሰው እውቀት ይለወጣል፣ ያድጋል፣ ይሰፋል፣ ይጎለምሳል፡፡ ወደደም ጠላም የሰው አካል የተፈጥሮውን ሂደት ጠብቆ ይለወጣል፣ ጽንሱ ይወለዳል፣ ሕጻኑ ያድጋል ወጣት ይሆናል፣ ወጣቱ ይጎለምሳል፣ ጎልማሳው ያረጃል፣ አካላዊ ጸባዩም በዚያው ልክ ይለወጣል፡፡ ትልቁ ፈተና መንፈሳዊ ለውጡስ የሚለው ላይ ሲደርስ ነው፡፡ መንፈሳዊ ለውጥ ከነዚህ ከሁለቱ ለውጦች የተለየ ነው፡፡ ተጋድሎ ከሥጋና ደም ጋር አይደለምና፡፡ የሰውየውን ታላቅ ጥረት፣ ሰማዕትነት እና የሃይማኖትን ጽናት የግድ ይላል፡፡ በዚህም የተነሳ በእውቀት ጎልምሰው፣ በዕድሜ አርጅተው፣ በመንፈሳዊ ለውጥ ግን ገና ሕጻናት የሆኑ ወይም ደግሞ በሕጸንነት እድሜ ላይ የጊዜ መቁጠሪያ ሰዓታቸውን ያቆሙ ብዙ ናቸው፡፡ ሌላው ቀርቶ ስለ መንፈሳዊ ሕይወትና ስለ ሃይማኖት እጅግ ብዙ የተማሩ በእውቀት ለሌሎች ሊተርፉ የሚችሉ ሌሎችን አስተምረው ለፍሬ ያበቁ ሰዎች በመንፈሳዊ ሕይወት ለውጣቸው ገና ወጣኒያን ሆነው የሚገኙበት አጋጣሚ አለ፡፡ ስለዚህም ሌላ የዘመን መለወጫ ከማክበራችን. አዲስ አመት ገባ እያልን ዶሮና በግ ከማረዳችን. እንደ ምዕራባውያውኑ ወደ ኋላሩ (Count down) ከመቁጠራችን በፊት ለቀጣዩ ጥያቄ መልስ እንፈልግ፡፡

ለውጥ በሌለው ሕይወት አቆጣጠር - ዛሬ ስንት ዓመተ ምሕረት ነው ?
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
www.melakuezezew.info - ስንክሳር ድረገጽ

Monday, August 18, 2014

አመታዊ የቅድስት ኪዳነ ምሕረት በዓል


እንኳን ለቅድስት ኪዳነ ምሕረት አመታዊ በዓል አደረሰን
“ወዳጄ ሆይ ተነሺ፣ ውበቴ ሆይ ነይ”
መኃ 2፡10

Sunday, August 3, 2014

ፍልሰታ ለማርያም

ፍልሰታ ለማርያም
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሐምሌ ፳፯ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ተዋዳጆች ሆይ! ዛሬ የምንማማረው በእንተ ፍልሰታ ለማርያም አይደለም፡፡ ስለ ራሳችን ፍልሰታ እንጂ፡፡ ኹላችንም ስለ እመቤታችን ፍልሰታ የመናገር ችግር የለብንም፡፡ ዛሬ እንድንማማርና እንድንወቃቀስ የፈለግኹት በሕይወታችን ከግብርናተ ዲያብሎስ ወደ ክርስቶስ ሳንፈልስ (ሳንሻገር) የእመቤታችንን ፍልሰታ ብቻ ለምናከብር ለየኔ ቢጤዎች ነው፡፡


እስኪ ከኹሉም አስቀድመን ለራሳችን ይኽን ጥያቄ እንጠይቀው፡፡ “በሕይወት ዘመኔ ስንት የፍልሰታ አፅዋማት አለፉ? እኔስ በዚኹ ጉዳይ ስንት ጊዜ ተናገርኩ? ስለዚኹ በዓል ለማወቅ መጓጓቴ ለማያውቁትም የማውቀውን ያኽል መናገሬ ክፋት ባይኖረውም እኔ ራሴስ ምን ለውጥ አመጣኁ? ምን ፍሬ አፈራኁ? ስለ ፍልሰታ እየተናገርኩ እኔ ራሴ ሳልፈልስ ስንት ዘመናት አለፉ? ከአገልግሎቴ ምን ረብሕ አገኛችኁ?”

ተወዳጆች ሆይ! እውነት ነው ምንም ሳንለወጥ ብዙ ዘመናትን አሳልፈናል፡፡ እኛ በሕይወት ሳንሻገር ብዙ የመሻገር (የፋሲካ) በዓላትን አክብረናል፡፡ እኛ ሳንነሣ ብዙ የመነሣት (የትንሣኤ) በዓላትን አክብረናል፡፡ እኛ በሕይወት ሳንፈልስ ብዙ የፍልሰታ በዓላትን አክብረናል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለእንደዚኹ ዓይነት ምልልሳችን እንዲኽ ነው የሚለን፡- “ቀንንና ወርን ዘመንንም ዓመትንም በጥንቃቄ ትጠብቃላችኁ፡፡ ምናልባት በከንቱ ለእናንተ ደክሜአለኹ ብዬ እፈራችኋለኹ” /ገላ.፬፡፲-፲፩/፡፡ በዓላትን የምናከብራቸው ቀናትን፣ ወራትን፣ ወይም ዘመናትን ለማክበር አይደለም፡፡ እነዚኽን በዓላት ምክንያት አድርገን ራሳችንን የበለጠ ወደ እግዚአብሔር ለማቅረብ ነው፡፡ እነዚኽን በዓላት ምክንያት አድርገን የእግዚአብሔር ቸርነቱን ለእኛም ያለውን ፍቅሩን ተረድተን እንድናመሰግነው ነው፡፡ ፍልሰታ ለማርያምን የምናከብረው በእመቤታችን ላይ የምንጨምረው ነገር ስላለ አይደለም፡፡ ፍልሰታን የምናከብረው እንደ እመቤታችን እንኳን ባይኾን የዓቅማችንን ያኽል በዚኽ ጊዜአዊ መቆያችን እስካለን ድረስ በንጽሕና በቅድስና ከምንም በላይ ደግሞ እግዚአብሔርን በፊደላት ሳይኾን በሕይወታችን ዐውቀነው አጣጥመነው የምንኖር ከኾነ ትንሣኤ፤ ፍልሰት እንዳለን እንድናውቅ ነው፡፡
ይኽን ግምት ውስጥ ባላስገባ መንገድ የምናከብረው ከኾነ ግን የእስከ አኹኑ ምልልሳችን አይሁዳዊ ምልልስ ነበር ማለት ነው፡፡ እንዴት? አይሁዳውያን ሕገ ኦሪትን የተሰጠቻቸው ኃጢአታቸውን በርሷ መስታወትነት ዐይተው ንስሐ እንዲገቡባት ስትሰጣቸው፥ እነርሱ ግን የንስሐ ፍሬ ሳያፈሩባት እንዲኹ ስለተመኩባት ለሕይወት የተሰጠቻቸው ሕግ ሞት ኾና አግኝቷታልና፡፡ እኛም እንዲኽ ለኵነኔ ያይደለ ለጽድቅ የተሰጠችን ወንጌል ፍሬ የማናፈራበት ከኾነ ክርስቶስን ከማያውቁ አይሁዳውያን የባስን ነን፡፡

እስኪ አንድ ምሳሌ አንሥተን እንማማር፡፡ አንድ የእግር ኳስ ክለብ በየጊዜው ተጋጣሚውን እንደምን ማሸነፍ እንዳለበት ልምምድ የሚያደርግ ከኾነ ክኅሎቱ ይዳብራል፡፡ ተጋጣሚውንም በቀላሉ ማሸነፍ ይቻሏል፡፡ በአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች የሚጫወቱ ክለቦች በየአገሩ እየዞሩ አቋማቸውን እየለኩ ያሉት በቀጣዩ ዓመት ለዋንጫ የሚያበቃቸውን ውጤት ለማምጣት እንጂ ተጨዋቾቹ ዕረፍት ማድረግ ስላልፈለጉ አይደለም፡፡ እኛስ! ፍልሰታን የምናከብረው ለምንድነው? እንደ እመቤታችን መነሣት እንዳለ እንድናውቅ ያንንም ሕይወት ገንዘብ ለማድረግ ወይስ እንዲኹ ልማድ ስለኾነብን? ለምንድነው የምንጦመው? ይኽ ጥያቄአችን ወደ ቀጣዩ መፍትሔ ያመራናል!!!

ክርስትና ጠቅላላ ዕውቀት አይደለም፤ እኛ በክርስቶስ ክርስቶስም በእኛ ኾኖ እግዚአብሔርን ማምለክ ነው እንጂ፡፡
እግዚአብሔርን ማምለክ ሲባልም በንግሥ በዓላት ላይ መሳተፍ፣ መዝሙር ወይም ማኅሌት ወይም ሰዓታት ላይ መሳተፍ፣ መጸለይ፣ መጦም፣ አስራት በኵራትን ማውጣት አይደለም፡፡ እነዚኽ ኹሉ ከእውነተኛ አምልኮአችን በኋላ የሚከተሉ ናቸው፡፡ ስለዚኽ እውነተኛ አምልኮ ከዚኽ የሚያልፍ (ከፍ የሚል) ነው፡፡ እውነተኛ አምልኮ እግዚአብሔር እኛን ምን ያኽል እንደሚያፈቅረን ማወቅ ነው፡፡
አዳም በኤደን ገነት ውስጥ ሳለ እግዚአብሔርን ያውቀው ነበር፤ መፍቀሬ ሰብእ እንደኾነ፡፡ በበደለ ጊዜ ግን ዓይነ ልቡናው ታወረ፡፡ እግዚአብሔር ስለ ፍቅሩ አዳምን ሲፈልገው ሲሸሽ የነበረውም በዚኹ ምክንያት ነው፡፡ ድምጹን እንኳን መስማት የተሳነው የእግዚአብሔርን ፍቅር አልረዳ ብሎ ነው /ዘፍ.፫፡፲/፡፡ እግዚአብሔር ግን በባሕርዩ ፍቅር ነውና ሰዎች ፍቅሩን እንረዳለት ዘንድ ይሻል፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳችንን በሙሉ ስናነብ የምንገነዘበው ነገር ቢኖር እግዚአብሔር ምን ያኽል የሰው ፍቅርን እንደተጠማ ነው፡፡ እግዚአብሔር አንድ አብርሃምን ሲፈልግ የነበረው፣ በቤቱ ውስጥ ገብቶ ማዕድን ሲበላ የነበረው፣ ከነ ይሥሐቅ ጋር የተወዳጀው፣ ከእነ ያዕቆብ ጋር ሲታገል ያደረው፣ ከእኔ ሙሴ ጋር በሲና ተራራ ፵ ቀንና ሌሊት ሲጨዋወት የነበረው ፍቅሩን የሚረዳለትና የሚያውቅለትን ሰው ፍለጋ ነው፡፡
እስራኤላውያን ፍቅሩን ይረዱለት ዘንድ ሕጉን በሙሴ በኵል ሰጣቸው፡፡ ሕጉም ገና ሲዠምር፡- “አነ ውእቱ እግዚአብሔር ዘአውፃእኩከ እምድረ ግብጽ እምቤተ ቅንየት - ጽኑ አገዛዝ ከምትገዛበት ከግብጽ አገር ያወጣኹኅ ፈጥሬ የምገዛኅ እግዚአብሔር እኔ ነኝ” ነው የሚለው /ዘጸ.20፡2/፡፡ እግዚአብሔር ከእኛ የሚሻው ተቀዳሚ ነገር ርሱን እንድናውቀው ነው ማለት ነው፡፡ ስናውቀው ፍቅሩን እንረዳለታለን፤ ደግሞም እንወዷለን፡፡ በነቢዩ ሆሴዕ አድሮ የተናገረውም ቢኾን፡- “ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን ከሚቃጠልም መሥዋዕት ይልቅ እግዚአብሔርን ማወቅ እወድዳለኹና” ነው የሚለው /ሆሴ.፮፡፮/፡፡ አስቀድመን እንደተናገርን ከመስገዳችን በፊት፣ ከመጦማችን በፊት፣ ከመጸለያችን በፊት፣ ሰዓታት ከመቆማችን በፊት፣ ሱባዔ ከመግባታችን በፊት እግዚአብሔር እንድናውቀው ይፈልጋል፡፡
ክብር ይግባውና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚኽ ምድር የመጣውም ለሌላ ዓላማ አይደለም፤ የሰው ፍቅር ጠምቶት እንጂ /ዮሐ.፬፡፯/፡፡ ጌታችን ከኀጢአት በቀር የእኛን ባሕርይ የተዋሐደው እኛ ከርሱ ጋራ እንድንዋሐድ ነው፡፡ የሰውነቱ ሕዋሳት ሲያደርገንም የአብ ፍቅሩ እንደምን ጥልቅ እንደኾነች እንድንረዳ ነው፡፡ አብ አንድያ ልጁን እስኪሰጠን ድረስ እንደወደደን እንድናውቅ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ በበዓለ ኃምሳ የተሰጠን ፍቅሩን ተረድተንለት በፍቅሩ ኖረን በእውነት ወዳጃችን እንደኾነ ዐውቀን በሕይወት እንድንኖርለት ነው፡፡ ልጅነትን አግኝተን በወይን ክርስቶስ ውስጥ ቅርንጫፍ የኾንነው የወልድን የባሕርይ ልጅነት በጸጋ ተካፋይ እንድንኾን ነው፡፡ አባ አባት ብለን እንጠራው ዘንድ የልጅነትን ሥልጣን የሰጠን ስለዚኹ ነው፡፡ በዚኽም ማንም ፍጥረት ሊደርስበት የማይችል የአባትነት ፍቅሩን እንድንረዳ ነው፡፡
በቅዱስ ቁርባን ክርስቶስ በእኛ እኛም በክርስቶስ ነው የምንኾነው፡፡ ከዚኽም የተነሣ አብን እናውቋለን፡፡ ምክንያቱም ከወልድ በቀር አብን የሚያውቀው ስለሌለ /ማቴ.፲፩፡፳፮/ ወልድ ደግሞ በለበሰው ሥጋ ከእኛ ጋራ ስለተዛመደና እኛም ከርሱ ጋራ ስለተዛመድን በርሱ በኩል እግዚአብሔር አብን እናውቋለን፡፡ ገና ስንዠምር እውነተኛ አምልኮ ያለውነውም በዚኹ ተፈጻሚነቱን ያገኛል፡፡
የሰው ልጆች አጥተነው የነበረው እውነተኛ ሥርዓተ አምልኮታችን በክርስቶስ (በቅዱስ ቁርባን) በኵል ተመልሶልናል፡፡ አስቀድመን እንደተናገርን ቀዳማዊ አዳም እግዚአብሔርን ከማወቅ ርቆ መታዘዝን እምቢ ብሎ ነበር፡፡ ክርስቶስ ግን ለአባቱ በመታዘዝ እውነተኛ አምልኮአችንን መልሶልናል፡፡
ርግጥ ነው በቅዱሳት መጻሕፍት እግዚአብሔርን እናውቋለን፡፡ በቅዱስ ቁርባን ግን በልጁ ደም ከርሱ ጋር እንታረቃለን፤ ርሱ በእኛ እኛም በርሱ እንኾናለንና ከየትኛውም መንገድ በላይ እናውቋለን፡፡ የኤማሁስ መንገደኞችን እናስታውሳቸው! የኤማሁስ መንገደኞች ጌታችን ከሙሴ እስከ ነቢያት ያሉ መጻሕፍትን ሲነግራቸው ልባቸው ይቃጠልባቸው ነበር፡፡ ከነርሱ ጋር እራት በበላ ጊዜ ግን ዓይኖቻቸው ተከፈተ፤ ክርስቶስንም ዐወቁት /ሉቃ.፳፬፡፴፪/፡፡
ታድያ እኛ እግዚአብሔርን በእውነት እያመለክነው ነው ወይ? በሌላ አገላለጥ ክርስቶስ በእኛ እኛም በክርስቶስ ውስጥ አለን ወይ? አብን ማወቅ የምንችለው የክርስቶስ ሕዋሳት የኾንን እንደኾነ ብቻ ነው፤ ወልድን የምናውቀው ብልቶቹ እንደኾንን ብቻ ነው፤ መንፈስ ቅዱስንም እንደዚኹ፡፡ ታድያ እግዚአብሔርን የምናወቀው በፊደላት ነው፥ ወይስ በእውነት በክርስቶስ ውስጥ ኾነን ማለትም ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን በመቀበል? በዚኽ ፍልሰታ ምን አስበናል አኹንም እንደ አምና እንዲኹ በዘልማድ ለማክበር? እንዲኽስ ከቶ አይኹን!!! እስኪ ከንስሐ አባቶቻችን ጋር እንማከርና ፍልሰታን በእውነት ፍልሰታ ለማርያም ብቻ ሳይኾን ለእኛም እናድርገው፡፡ ይኽን እንድናደርግ የእግዚአብሔር ቸርነት የእመቤታችን አማላጅነት የቅዱሳን መላዕክት ተራዳኢነት ይርዳን አሜን!!!