Sunday, April 14, 2013

ገብርኄር


በዲ/ን አባተ አስፋ
ዛሬ ታላቁን የጌታችንን ጾም ከጀመርን ስድስተኛ ሳምንት ላይ ደርሰናል፡፡ ይህን ሳምንት ቅድስት ቤተክርስቲያን «ገብርኄር» የሚል ስያሜ ሰጥታዋለች፡፡ ገብርኄር በጎ አገልጋይ ማለት ሲሆን የስያሜውን መነሻ የምናገኘው በዕለቱ ሥርዓተ ቅዳሴ ከሚነበበው የወንጌል ክፍል ማቴ.25-14-30 ነው፡፡
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምሳሌ መስሎ ካስተማራቸው ትምህርቶች መካከል አንዱ የሆነው ይህ የዛሬው ወንጌል አስተማሪ የሆኑ መሠረታዊ ጉዳዮችን በውስጡ ይዟል፡፡ በተለይ ምንም እንኳን የቤተክርስቲያን ሓላፊነት የእገሌና የእገሊት ተበሎ ባይወሰንም ቤተ ክርስቲያን ባላት የአገልግሎት መዋቅር መሠረት የሓላፊነትን ቦታ ይዘው ለሚያገለግሉ ሰዎች አትኩሮት ሊሰጡባቸው የሚገባቸውን ነጥቦች ይጠቁማል፡፡ ይህን ለማየት ያመቸን ዘንድ ከታሪኩ የመጀመያ ክፍል በመነሣት ዋና ዋና የሆኑ ዐሳቦችን በአትኩሮት መመርመር ጠቃሚ ነው፡፡

Sunday, April 7, 2013

ደብረ ዘይት


በአባ ዘሚካኤል ደሬሳ
የዓለሙ ፍጻሜ ምልክቱ ምንድ ነው?/ማቴ. 24፣3/

በዓቢይ ጾም ውስጥ ካሉት ሳምንታት ደብረ ዘይት 5ኛው ሳምንት ላይ ይውላል፡፡ ደብረ ዘይት ትርጉሙ የወይራ ዛፍ ተራራ ማለት ሲሆን፣ ይህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኢየሩሳሌም በሚገኘው በደብረ ዘይት ተራራ ቅዱሳን ሐዋርያት” የዓለሙ ፍጻሜስ ምልክቱ ምንድነው?”/ማቴ. 24፣3/ ብለው ጠይቀውት እርሱም የማይቀረውን የዓለም ፍጻሜና አስቀድመው የሚፈጸሙ ምልክቶችን አስረድቷቸዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ይህንኑ በደብረ ዘይት ሳምንት ታስበዋለች፤ ለምእመናኑም ከዘመኑ ሁኔታ አንጻር በመጻሕፍት የተጠቀሱትን የትንቢት ምልክቶቹን ከተግባራዊ የዓለም ክንዋኔዎች አንጻር በማገናዘብ ታስተምራለች፡፡ በመሆኑም በቤተ ክርስቲያናችን በደብረ ዘይት ሳምንት ምጽአትን አስመልክቶ የሚነገሩ ምስጢራት እጅግ ሰፊ ናቸው፡፡ ነገር ግን በዚህ ጽሑፍ በመጠኑ የምናየው ከቅዱሳት መጻሕፍት አንጻር በዓለም እየተከሰቱ ካሉ ወቅታዊ ምልክቶች ጋር በማገናዘብ ይሆናል፡፡

Tuesday, March 12, 2013

አርባ መአልትና አርባ ሌሊት ጾመ ማቴ.4፥2


በመ/ር ምሥጢረሥላሴ ማናየ
ይህ ከላይ ያነሣነው ርዕስ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችንና አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አርባ መአልትና አርባ ሌሊት መጾሙን ያስተምረናል፡፡
በዚህ ኀይለ ቃል ሁለት ታላላቅ ቁም ነገሮችን ቃላትን እንመለከታለን

  1. አርባ መአልትና አርባ ሌሊት
  2. ጾም የሚሉት ናቸው፡፡

በቅድሚያ አርባ መአልትና አርባ ሌሊት የሚለውን ከእነ ምስጢሩ እንመለከተዋለን፡፡ ቀጥለን ደግሞ ጌታችንስ ለምን አርባ መአልትና አርባ ሌሊት ጾመ? የሚለውን እንመለከታለን እግዚአብሔር አይነልቡናችንን ይክፈትልን፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን የፈጠረውን የሰው ልጆችን አባት አዳምን፣ በልጅነት አክብሮ ገነት ያስገባው በፈጠረው በአርባ ቀኑ ነው፡፡ “ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ እግዚአብሔር ዘገብሮ ለአዳም” አዳምን የፈጠረ እግዚአብሔር ቅዱስ ነው እያሉ እያመሰገኑ መላእክት ወደገነት አስገብተውታል /ቀሌ.4፥/

Saturday, March 9, 2013

የዐቢይ ጾም ስብከት


በአያሌው ዘኢየሱስ

ሐዋርያዊትና ኦርቶዶክሳዊት በሆነችው በቅድስቲቱ ቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ጾም እንደ እንግዳ ደራሽ፤እንደ ወንዝም ፈሳሽ በድንገት የተጀመረ ሥርዓተ አይደለም፡፡ በተለይም በአዲስ ኪዳን ዘመን ጾም ሰው ሠራሽ ሕግ ሳይሆን መድኀኒታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ የመጀመሪያ አድርጎ የሠራው ሕግ ነው፡፡ ጌታ በመዋዕለ ስብከቱ በአንድ ወቅት ከመጥምቁ ዮሐንስና ደቀ መዛሙርት ጾምን አስመልክቶ የቀረበለት ጥያቄና የሰጠው መልስ አለ፡፡ ያቀረቡለት ጥያቄ፡- «. . .  እኛና ፈሪሳውያን ብዙ ጊዜ የምንጦመው፤ ደቀ መዛሙርትህ ግን የማይጦሙት ለምንድር ነው?» (ማቴ 914)  የሚል ነበር፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጣቸው መልስ እንዲህ የሚል ነበር፡- «. . . ሚዜዎች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ ይችላሉን; ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል፤በዚያን ጊዜም ይጦማሉ፡፡» ማቴ 915፡፡ ጌታ በዚህ መልሱ ውስጥ ራሱን  በሙሽራ ደቀ መዛሙርቱንም በሚዜዎች በመመሰል እርሱ በመንፈስ ሳይሆን በሥጋ ከእነርሱ በዕርገቱ ተለይቶ ከመሔዱ በፊት ሊያዝኑ፣ ሊተክዙና ከመባልዕት ሊከለከሉ እንደማይችሉ ነገር ግን በዕርገቱ ሲለያቸው መጾም እንደሚጀምሩ ተናገረ፤አስተማረ፡፡ በመሆኑም «በዚያን ጊዜም ይጦማሉ፡፡» የሚለው ሐረግ እርሱ በገዳመ ቆሮንቶስ የጣለውን የጾም መሠረት እነርሱ ከዕርገቱ በኋላ አጠናክረው እንደሚቀጥሉበት የሚያጎላ ነው፡፡

Monday, February 25, 2013

ፍርድ ለነነዌ÷ ሥልጣን ለነነዌ




በዲ/ን ዮሴፍ ይኩኖአምላክ

ኮናኔ በርትዕ÷ ፈታሄ በጽድቅ÷ የሆነው መድኀኒዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ጻፍት ፈሪሳውያንን በቋንቋቸው በዕብራያስጥ ቢያስተምራቸው “እንደ ሙሴ፡- ባሕር ከፍለህ÷ ጠላት ገድለህ÷ ደመና ጋርደህ÷ መና አውርደህ፣ እንደ ኢያሱ፡- በረድ አዝንመህ÷ ፀሐይ አቁመህ÷ እንደ ጌዴዎን፡- ፀምር ዘርግተህ ጠል አውርደህ፣ እንደ ኤልያስ ሰማይ ለጉመህ እሳት አዝንመህ ልታሳየን እንወዳለን” የሚል ጥያቄ በቀረበለት ጊዜ የሰጣቸው ምላሽ “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል÷ ከነቢዩ ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት  አይሰጠውም፡፡ ዮናስ በዓሣ አንበሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ÷ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል፡፡ የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈረዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና÷ እነሆም ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ” የሚል ነው፡፡ ጻፍት ፈሪሳውያንን ምልክት ያስፈለጋቸው ዋነኛ ምክንያት በጌታችንና በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት ለማመን አልነበረም፤ ይልቅስ እንደ ዘማ ሴት ምልክት በምልክት እየተደራረበ ማየትን በመናፈቅ ነው፡፡

Friday, February 15, 2013

የየካቲት ኪዳነ ምህረት ዓመታዊ ክብረ በዓል

                                      በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! 

በሀገረ ቤልጅየምና በዙሪያዋ ለምትኖሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምእመናን በሙሉ፤  

 በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በእናታችን በወላዲተ አምላክ ቅድስት ድንግል ማርያም ስም መንፈሳዊ  ሰላምታችንን እያስቀደምን: እንኳን ለእናታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ ክብረ በዓል በሠላም አደረሳችሁ። የካቲት ኪዳነ ምህረትን በዓል በዕለቱ የካቲት 16 2005. (Feb 23, 2013) ከዋዜማው (የካቲት15, Feb.23) ጀምሮ; ከየአጥቢያ ቤተክርስቲያን ሚመጡ አባቶች ና ምእመናን በሚገኙበት ሌሊት በማኅሌት እና  ጠዋት በቅዳሴ በደመቀ ሁኔታ ይከበራል። ቤተክርስትያኗ ከዋዜማው ምሽት 22፡00 ሰዓት ጀምሮ ክፍት ስለምትሆን በሰዓቱ ተገኝተው ከልዩ ልዩ የአዳር መርሐ ግብሮች ተካፋይ እንዲሆኑና ሌሎችንም እንዲጋብዙ ቅድስትቤተ-ክርስቲያን ጥሪዋን ታስተላልፋለች።  ሕንፃ ቤተ-ክርስትያኑ ከእኩለ ቀን (11፡30) በሗላ ለሌላ አገልግሎት ስለሚፈለግ በሰዓቱ ቀደም ብለው በመገኘት የበረከቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ በትህትና እንጋብዛለን።   ይህ መልዕክት የማይደርሳቸውን ምዕመናንንም በመቀስቀስ የበረከቱ ተሳታፊ እናድርጋቸው።             

 የአምላካችን ረድኤት የቅድስት ኪዳነ ምሕረት አማላጅነት ከሁላችን ጋር ይሁን።

Tuesday, February 5, 2013

“የዲያብሎስን ሥራ ይሽር ዘንድ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ፡፡” 1ኛ ዮሐን.3፥8




ምንጭ :ከማህበረ ቅዱን ድህረ ገፅ የተወሰደ
በዲ/ን ኃይለ ኢየሱስ ቢያ
ይህንን ኀይለ ቃል የተናገረው  ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ነው፡፡ የተናገረበት ምክንያት፡-
የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ የጌታችን መድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ /ሰው ሆኖ የማዳን ሥራውን/ መፈጸሙን ለመግለጥ  የተናገረው /የጻፈው ኀይለ ቃል ነው፡፡
  • መገለጥ ማለት ፡- ረቂቁ አምላክ በተአቅቦ ርቀቱን ሣይለቅ ውሱን ሥጋን ውሱኑም ሥጋ በተአቅቦ ውስንነቱን ሳይለቅ ረቂቅ መለኮትን የሆነበት በአጭር ቃል የቃል ግብር ለሥጋ የሥጋ ግብር ለቃል የሆነበት ረቂቅ ምስጢር ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ቀዳማዊ ደኃራዊ የሆነው አምላክ ሞት የሚስማማው ሆነ፤ ዘመን የሚቆጠርለት ሥጋ ዘመን የማይቆጠርለት ሆነ፡፡ ሥጋ በማይመረመር ምስጢር የመለኮትን ገንዘብ ገንዘቡ ቢያደርግ “ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ ሞቼም ነበርሁ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ” /ራእ.1፥17/ ማለት የቻለበት ምስጢር ነው፡፡ የረቀቀው ገዝፎ የገዘፈው ረቆ፣ ሰማያዊው ምድራዊ  ምድራዊው ሰማያዊ ሆኖ መታየት ማለት ነው፣  ከዓለም ተሰውሮ የነበረው ምስጢር  ግልጥ ሆኖ መታየት ማለት ነው ይህንንም ምሥጢር ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በጢሞቴዎስ  መልእክቱ “እግዚአብሔርን የመምሰል ምስጢር ያለጥርጥር ታላቅ ነው፤ በሥጋ የጠገለጠ፣ በመንፈስ የጸደቀ፣ ለመላእክት የታየ፣ በአሕዛብ የተሰበከ፣ በዓለም የታመነ፣ በክብር ያረገ /1ጢሞ 3፥16/ በማለት፡፡ ከልደት እስከ ዓቢይ ጾም መጀመሪያ  ያለው ጊዜ  ዘመነ አስተርእዮ /የመገለጥ ዘመን/ የመታየት ወቅት ይባላል::

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ በፍጹም ተዋሕዶ ሰው መሆኑን /ዓለምን ለማዳን መወለዱን የምንገልጽበት ወቅት ነው፡፡

የእግዚአብሔር መገለጥም በ3 ዘመናት ከፍሎ ማየት ይቻላል