✍ በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ
❖
✔ በረከቱ ይደርብንና የነቢዩ ኤልሳዕ በዐለ ዕረፍት ጥቅምት 20 ሲኾን፤ የኤልያስ መንፈስ ዕጥፍ የኾነለት፤ የኢያሪኮን ውሃ በጨው ያጣፈጠ ነው፤ ጨው የጌታ፤ ዐዲስ ማድጋ የእመቤታችን ምሳሌ ነው፤ በፍዳ በመርገም የመረረችውን ዓለም ያጣፈጠ የዓለም መድኀኒት ክርስቶስን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና ወልዳ ያስገኘችልን እናታችን ድንግል ማርያምም የኢያሪኮን ውሃ ምረት ያስወገደውን ጨው በያዘችው በኤልሳዕ ዐዲስ ማሰሮ ትመሰላለች (፪ነገ ፪፥፳)፡፡
♥❖
✔ ነቢየ እግዚአብሔር ኤልሳዕ መምህሩ ኤልያስን ሸኝቶ ዮርዳኖስን ተሸግሮ ኢያሪኮ ደረሰ፤ ወደዚያው ገብቶ “ሠናይት ንብረታ ለዛቲ ሀገር” አለ፤ የከተማይቱም ሰዎች ኤልሳዕን “እነሆ ጌታችን እንደሚታይ የዚች ከተማ ኑሮ መልካም ነው” ወማየ ብሔሩሰ እኩይ ውእቱ የአገሩ ውሃ ግን ክፉ ነው፤ "አንስትኒ ይመክና" ወላዶች ሴቶች ሲጠጡት ይመክናሉ ደኽነኛው ሰውም ቢጠጣው በሽተኛ ይኾናል አሉት።
❖
✔ኤልሳዕም “በውስጡ ጨው ጨምራቸው ዐዲስ ማሰሮ አምጡልኝ” አላቸው፤ እነሱም አመጡለት፤ ኤልሳዕም ውሃው ወዳለበት ምንጭ ወጥቶ፤ ጨው ጨምሮ ማሰሮውን ከቀበረ በኋላ “እግዚአብሔር እንዲኽ ይላል ይኽነን ውሃ ፈውሼዋለኊ፤ ከዚኽም በኋላ ሞትና ጭንገፋ አይኾንበትም” አለ፡፡ ከዚያ ቀን ዠምሮ ውሃው ከምረቱ ተለውጦ ጣፍጦ በሽተኛ ቢጠጣው ጤነኛ፤ መካን ብትጠጣው የሚያስወልድ ኹኗል (፪ነገ ፪፥፲፱-፳፪)፡፡
✔❖
♥ ለጊዜው እንዲኽ ተደርጓል ለኋላው ግን ምሳሌ ነበር፤ የውሃውን ምረት ያጠፋውን ጨው የያዘችው ዐዲስ ማሰሮ፤ ከዓለም ፍዳ መርገምን ያጠፋ ጌታን የወለደች የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ስትኾን፤ ጨዉ የጌታ፤ ውሃው የዚኽ ዓለም፤ ምረት የፍዳ የመርገም ምሳሌ ነበር፡፡
✔❖ ኢትዮጵያዊዉ ሊቅ አባ ጊዮርጊስም ይኽነን ልዩ ምሳሌ ሲተረጒም "ኤልሳዕ ካዕበተ መንፈሱ ለሊቁ ነሥአ …” (ኤልሳዕም በመምህሩ ያደረ መንፈስ ቅዱስን ዕጥፍ ድርብ አድርጎ ተቀበለ፤ በመጠምጠሚያውም ምት የዮርዳኖስን ባሕር ከፈለው፤ የመጥረቢያውን ብረትም በውሃ ላይ አንሳፈፈው፤ ብዙ ተአምርንም ዐደረገ፤ ሙታንን አነሣ፤ በዮርዳኖስ ውሃ ለምጻሙ ንእማንን አነጻው፤ የሚያመክነውንም የውሃ ምረት በጨው አጣፈጠ፤ መካኖች የሚኾኑ የዚያ ሀገር ሰዎች ይወልዱ ዘንድ (፪ነገ ፪፥፲፱-፳፩፤ ፭፥፲፬፤ ፮፥፮-፯)፤ ከኀጢአት ማንጻትን የነፍስንም ምረት ማጣፈጥን ግን አልቻለም፤ ልጅሽ ግን የሥጋ ለምጻሞችን አነጻቸው፤ ዳግመኛም የዓለሙን ምረት በመለኮቱ ጨውነት አጣፈጠ፤ ኹለተኛም ውሃውን አጣፍጦ የወይን ጠጅ ዐደረገው) (ማቴ ፰፥፪-፫፤ ዮሐ ፪፥፰-፱)) ፤ በማለት ለ፭ሺሕ ፭፻ ዘመን ከመድኀኒቷ ተለይታ፤ አልጫ ለኾነችው ዓለም መድኀኒት የኾነ መድኀኔዓለም ክርስቶስን ያስገኘችልን መኾኗን አስተምሯል፡፡
♥❖
✔ ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬምም በመጽሐፉ ላይ ይኽነን ሲያብራራ ‹‹አንቺን በሐዲስቱ ማሰሮ ገለጠሽ፤ ልጅሽም ለምንጩ ዐዲስ ሕይወትን የሰጠ ጨው ነው፤ በሱም ሙታ የነበረችው መላዋ ዓለም እንደገና ሕይወትን አገኘች ›› በማለት ለ፭ሺሕ ፭፻ ዘመን በመሪር መርገም ሥር ወድቃ ሕይወቷን ላጣችው ዓለም ሕይወት የኾናትን ክርስቶስን ያገኘንባት ዐዲሲቱ ሸክላ ቅድስት ድንግል መኾኗን መስክሯል፡፡
♥❖
✔ ሊቁ ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግም በልደት ድርሳኑ ላይ ይኽነንኑ ሲመሰክር ‹‹The new pitcher of Elisha has been explained to us…›› (ዐዲሲቱ የኤልሳዕ ጋን ምሳሌነቷ ምድርን ያረጋጋች የድንግል ምሳሌ እንደኾነች ለእኛ በግልጽ ታወቀ፤ በምንጩ ውስጥ የተጨመረው ጨውም የእግዚአብሔር ልጅ ነው፤ ርሱም ባልጣፈጠው ማንነታችን ላይ ጣዕሙን የጨመረልን ነው) በማለት እመቤታችንን በማሰሮዋ፤ ጌታን ውሃውን ባጣፈጠው ጨው በመመሰል፤ በጌታ ሰው መኾን የሰው ልጆች ድኅነት እንዳገኙ በጥልቀት ተናግሯል፡፡
♥❖ በቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ የነገረ ማርያም አስተምህሮ ላይ ጥልቅ ጥናት ያጠናው የነገረ መለኮት ምሁሩ ጀምስ ይኽነን የቅዱስ ያዕቆብ ቃልን ሲያብራራ "The symbol of the ‘‘New pitcher of Elisha’’ is the best symbol…›" (ዐዲስቱ የኤልሳዕ ጋን ቅዱስ ያዕቆብ የድኅነትን ጭብጥ መልእክት የድኅነትን ተስፋ ካሳየባቸው ምሳሌዎች ዋነኛዋ ናት፤ የጥሩ ውሃ ዕጦትና የፍሬ የለሿ ምድር፤ ኤልሳዕ ይኽነን ተአምር እንዲሠራ ሥር መሠረቱ ነበረች፤ ይኽም ኀጢአትን የተመላ የሰዎችን ኹኔታ ይመስላል፤ በሐዲስቱ ሸክላ ያለ ይኽ ጨው የሕዝቡን ኹኔታ ለወጠ፤ ይኽም ድርጊት ወደፊት ሊመጣ ያለውን የጌታ የሰው ዘርን የማዳን ውጤትን ያሳየ ነው፤ ይኽም ምልክት ድንግል ማርያም በነገረ ድኅነት ያላትን ድርሻ የሚጠቁመን ነው፤ የሕዝቡን አኗኗር የለወጠው ጨው ነው፤ ግን ጨው የተቀመጠው በዐዲስ ሸክላ ነው፤ ቅዱሳት መጻሕፍት ስናነብ ክርስቶስ እኛን እንዳዳነ ይናገራል፤ ይኸውም በሐዋ ሥራ ምዕ ፬፥፲፪ ላይ ‹‹መዳንም በሌላ በማንም የለም እንድንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና›› ሲል፤ በሕዝቡ የነበረው አኗኗር ኹኔታ የተለወጠው በክርስቶስ (በጨዉ) ሲኾን፤ ማርያምም (ዐዲሲቱ ሸክላ) ለሰው ዘር ኹሉ ያንን ጨው (ጌታን) የሰጠችን (ያስገኘችልን) ናት፤ በመኾኑም ይኽ ምልክት ከድንግል ማርያም የአምላክ እናትነቷ ምስጢር ጋር የሥጋዌና የድኅነትን ምስጢር በግልጽ ያሳያል) ሲል የሰው ዘር ኹሉ ተስፋነቷንና ነገረ ክርስቶስ (Christology) ከነገረ ማርያም (Mariology) ጋር ያለውን ጥብቅ ትስስር ገልጾታል፡፡
❖
✔ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስን ያጠፋ፤ በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስን ያደለ ጌታን የወለደችልን እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የውሃውን ምረት ያስወገደውን ጨው በያዘችው ሸክላ ብቻ ሳይኾን፤ የቅጠሉ ምረት በተወገደባት በኤልሳዕ ማድጋ ትመሰላለች (፪ነገ ፬፥፴፰-፵፩)።
♥
✔ ይኸውም በዘመነ ረኀብ ደቂቀ ነቢያት ተሰብስበው ወደ ኤልሳዕ ኼዱ፤ ርሱም ደቀ መዝሙሩ ግያዝን ጠርቶ “ታላቅ ማድጋ ጥደኽ ለነቢያት ልጆች ቅጠል ለቅመኽ ቀቅለኽ ስጣቸው” አለው፤ ርሱም ክፉና በጎ ሳይለይ ለቅሞ አምጥቶ ሰጣቸው፤ እነሱም በቀመሱት ጊዜ “የእግዚአብሔር ሰው ሆይ በማድጋው ውስጥ ሞት አለ” ብለው ጮኹ፤ ከምረቱም የተነሣ መብላት ተሳናቸው፤ ኤልሳዕም “የስንዴ ዶቄት አምጥተኽ አላትነኽ ስጣቸው” አለው፤ርሱም አላትኖ ቢሰጣቸው ምረቱ ጠፍቶላቸው ጣፍጧቸው ተመግበዋል፤ ከዚኽ በኋላ በምንቸቱ ውስጥ ምሬት አልተገኘም፡፡
♥
✔ ይኽም ለጊዜው ተደርጓል፤ ለኋላው ግን ምሳሌ ነው፤ ማድጋ የድንግል ማርያም፤ ቅጠል የትስብእት፤ ላተን የመለኮት፤ ምረት የፍዳ የመርገም ምሳሌ ነውና፤ ክብር ይግባውና መድኀኔ ዓለም ክርስቶስ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስን ነሥቶ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስን በመሻሩ ሊቃውንት ቅድስት ድንግል ማርያምን በኤልሳዕ ማድጋ መስለዋታል፤ ሊቁ አባ ሕርያቆስም በቅዳሴ ማርያም በቊ ፴፭ ላይ ይኽነን ምስጢር በመያዝ "መስብክት ዘኤልሳዕ" (የኤልሳዕ ማድጋ አንቺ ነሽ) በማለት አመስግኗታል፡፡
❖
♥ እኔም እስራኤል ኼጄ ኢያሪኮን በጐበኘኹበት ጊዜ ነቢዩ ኤልሳዕ ካጣፈጣት ጣፍጭ የበረከት ውሃ ተጠምቄ ከምንጯ በመጠጣቴ ልዩ ደስታን ኹሌ ይሰማኛልና፤ ቅዱስ ኤልሳዕን በሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም ምስጋና እንዲኽ ስል አወድሰዋለኊ፡-
“ሰላም ለኤልሳዕ ነቢይ ዘኀይለ ጸሎቱ ዐቢይ ዘዐቀመ ማየ ዮርዳኖስ ለፌ ወለፌ፤ በቅርፍተ ዕፅ እማይ ዘአውጽአ ማሕጼ፤ ዘረሰያ ለማይ መሪር ጥዕምተ፤ መዊቶሂ ዘአንሥአ በድነ ምውተ”፡፡
(የጸሎቱ ኀይል ደገኛ የኾነ፤ የዮርዳኖስን ወንዝ ወዲያና ወዲኽ ያቆመ፤ በዕንጨት ቅርፊትም ከውሃ ውስጥ መጥረቢያን ያወጣ፤ መሪር ውሃን ጣፋጭን ያደረገ፤ ሙቶ ስንኳ የሙቱን በድን ላነሣው ለነቢዩ ለኤልሳዕ ሰላምታ ይገባል) አሜን፡፡
ምንጭ፡- ነገረ ማርያም በብሉይ ኪዳን ክፍል አንድ የሚለው መጽሐፌ
ከመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ
[ቅዱስ ኤልሳዕ የኢያሪኮን መራር ውሃ በጸሎቱ እንዳጣፈጠ፤ ዛሬም በምልጃው ሕይወታችንን የጣፈጠ ያድርግልን]፡፡
No comments:
Post a Comment