Pages
▼
ጽድቅን መከተል
ጽድቅ
እያንዳንዱ ሰው ወደ ክርስቲያናዊ ፍጹምነት በሚያደርገው ጉዞ ሊያፈራው የሚገባ ፍሬ ነው፡፡ ‹‹መልካም ፍሬ
የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቈረጣል ወደ እሳትም ይጣላል።›› (ማቴ.፫÷፲) ጌታችን ስለ እነዚህ ፍሬዎች ጥቅም የነገረንም
ይህንኑ ነው፡፡ ከመቀጠላችንም በፊት ጌታችን የነገረንን ተጨማሪ ነገር እንስማ ፡-‹‹በእኔ ኑሩ እኔም በእናንተ።
ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ባይኖር ከራሱ ፍሬ ሊያፈራ እንዳይቻለው፥ እንዲሁ እናንተ ደግሞ በእኔ ባትኖሩ አትችሉም።
እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና በእኔ የሚኖር እኔም
በእርሱ፥ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል።›› (ዮሐ. ፭÷፬—፭) እናም ፍሬን ለማፍራት የመጀመሪያው መመሪያ ይህ ነው፡፡
‹‹ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉም፡፡›› ማንም ሰው በራሱ ጥረት ብቻ ሊያፈራ አይችልም፡፡ ፍሬያማዎች
የሚያደርገን እርሱ እግዚአብሔር ነው፡፡
እግዚአብሔር መሬት እንዳለውና መሬቱን እንዲንከባከቡ
አገልጋዮችን እንደቀጠረ ገበሬ ነው፡፡ መሬቱና ዘሩ የእግዚአብሔር ነው ፤ ማዳበሪያውም እንዲሁ ነው፡፡ እግዚአብሔር
ለእርሻ የሚያስፈልገውን ዝናምና ፀሐይም ያዘጋጃል፡፡ የተቀጠረው አገልጋይ ደግሞ በሚገባ ማረስ ፣ ዘርን መዝራት ፣
አረምን ማረም ፣ ማዳበሪያን ማድረግና የድካሙን ዋጋ ማጨድ ይጠበቅበታል፡፡ ነገር ግን የቅጥረኛው ሠራተኛ ሥራውን
ከመሥራት በስተቀር በሠራው ነገር ላይ መብት የለውም፡፡ በእኛም እንዲሁ ነው ‹‹እንዲሁ እናንተ ደግሞ የታዘዛችሁትን
ሁሉ ባደረጋችሁ ጊዜ። የማንጠቅም ባሪያዎች ነን፥ ልናደርገው የሚገባንን አድርገናል በሉ።›› እንዳለን ጌታችን፡፡ (ሉቃ. ፲፯÷፲)
ቅድስና እንዲሁ አይከሰትም፡፡ አንድ ሰው በተገቢው መንገድ ቅድስናን ለማግኘት መለማመድ አለበት፡፡ አንዳንድ ጊዜ
በጎነት ከምድር እስከ ሰማይ በሚደርስና ብዙ ደረጃዎች ባለው መሰላል ይመሰላል፡፡ አንዳንድ በጎነቶች በመሰላሉ ከሥር
ሲገኙ ሌሎች ደግሞ
ከመሰላሉ ጫፍ ላይ ይገኛሉ፡፡ አባቶች እነዚህን መሰላሎች ዘልለን ልናልፋቸው አንችልም
ነገር ግን ደረጃ በደረጃ ልንወጣቸው ይገባናል ይላሉ፡፡ በታችኛው የመሰላሉ መውጫ ላይ ሁለት መሠረታዊ የሆኑ የጽድቅ
ሥራዎች አሉ፡፡ እነዚህም መታዘዝና ትእግሥት ናቸው፡፡
በመሰላሉ የላይኛው ጫፍ ላይ ደግሞ ትሕትናና ፍቅር አሉ፡፡ ፍቅር ከሁሉም የበጎነት ደረጃዎች ከፍተኛው ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜም ‹ሁሉን የሚያጠቃልል በጎነት› ተብሎ ይጠራል፡፡
ፍቅር ያለው ሁሉም በጎነቶች ይኖሩታል፡፡ በጎነትን ስንለማመድ አንድ በአንድ ልንለምዳቸው እንደሚገባን ይመከራል፡፡
አንዱን የበጎነት ደረጃ ተለማምደን ስንጨርስ የመሰላሉን ቀጣይ ደረጃ ደግሞ እንወጣለን፡፡ በጎነት በየጊዜው
እየዳበረ የሚሔድ ነገር ነው፡፡ አንዱን
በጎነት መልመድ የሚቀጥለውን በጎነት በቀላሉ ለማግኘት ያስችላል፡፡
ለምሳሌ ራስህን ትእግሥትንና መታዘዝን ካስለመድኸው የዋህነትም የአንተ ይሆናል፡፡ የዋህነትን ስትይዝ ደግሞ በትሕትና
ደጃፍ ላይ ነህ እንዲህ እያለ ይቀጥላል፡፡
አንድ ልምምድ አለማማጅ ወይም አሰልጣኝ ይፈልጋል፡፡
ማንም ሰው ያለ አሰልጣኝ በአትሌቲክስ ሊሳካለት አይችልም፡፡ እንዲሁም አንድ ክርስቲያን ያለ አሰልጣኝ ‹የክርስቶስ
/መንፈሳዊ/ ሯጭ› ሊሆን አይችልም፡፡ አሰልጣኝህ ደግሞ የንስሐ አባትህ ናቸው፡፡ በልምምድህ ወቅትም ትእዛዝ ሊሰጡህ
የሚገባው እርሳቸው ናቸው፡፡ ያለፈውን ምእራፍ አንብበኸውና ተረድተኸው ከሆነ በእርግጠኝነት ይህን ልምምድ በራስህ
የማድረግህን አደጋ ትረዳዋለህ፡፡ ታዛዥነትና ትእግሥት ሌሎች በጎነቶችን ለማግኘት እንደ ቅድመ ሁኔታ የሚቆጠሩ
ናቸው፡፡ እነዚህን መሠረታዊ በጎነቶች ካልያዝህ ሌሎች የበጎነት ፍሬዎችን ልታፈራ አትችልም፡፡ የዚህም ምክንያቱ
ታዛዥ ካልሆንህ በአሰልጣኝህ /በንስሐ አባትህ/ የሚሰጥህን ትእዛዝ ልትፈጽም አትችልም፡፡ በእርግጥም ምንም ዓይነት
እድገት አይኖርህም፡፡ እንዲሁም ትእግሥት ሳይኖርህ ልምምድህን በጽናት ለማካሔድና ፍሬ ለማፍራት አትችልም፡፡ በዘር
ዘሪው ምሳሌ ላይ ጌታችን እንዲህ ሲል ነግሮናል ፡- ‹‹በመልካም መሬት ላይም የወደቀ እነርሱ በመልካምና በበጎ ልብ
ቃሉን ሰምተው የሚጠብቁት በመጽናትም ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው።››
(ሉቃ. ፰÷፲፭)
ምንጭ ተግባራዊ ክርስትና
ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ እንደተረጎመው
No comments:
Post a Comment