Tuesday, July 30, 2013

የአብርሃም ዛፍና የአብርሃም ድንኳን

በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ
ነገረ ማርያም በብሉይ ኪዳን ከሚለው መጽሐፍ የተወሰደ 



እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እግዚአብሔር ለአብርሃም በአንድነት በሦስትነት በተገለጠባት ዛፍና፤ በገባበት ድንኳን ትመሰላለች (ዘፍ ፲፰፥፩-፴፫)፡:

ይኸውም አብርሃም ከደግነቱ ብዛት እንግዳን ከመውደዱ የተነሣ ድንኳኑን በተመሳቀለ ጎዳና ሠርቶ የወጣ የወረደውን ያለፈ ያገደመውን ሲቀበል የሚኖር በሥራው ኹሉ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ጻድቅ ነበር (ሮሜ ፬፥፩-፫)፡፡ ጽድቁም ሊታወቅ ስድስት ሰዓት ላይ አብርሃም በድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ፤ በመምሬ ዛፍ ሥር እግዚአብሔር በአንድነት በሦስትነት ተገለጸለት ‹‹ወሶበ አልዐለ አብርሃም አዕይንቲሁ ነጸረ ሠለስተ ዕደወ እለ ይቀውሙ ወርእየ ወሮጸ ለተቀብሎቶሙ እምኆኅተ ኅይመት ወሰገደ ውስተ ምድር›› ይላል ዐይኑን አቅንቶ ሲመለከት፤ ሥላሴ በአምሳለ ዕደው ቆመው አይቶ፤ ሊቀበላቸው ከድንኳኑ ደጃፍ ተነሥቶ ሮጠ፤ ወደ ምድርም ሰገደ፤ ከዚኽ በኋላ ‹‹አቤቱ በፊትኽስ ሞገስ አግኝቼ እንደኾነ ባሪያኽን አትለፈኝ ብዬ እለምናለኍ፤ ጥቂት ውሃ ይምጣላችኍ፤ እግራችኹን ታጠቡ፤ ከዚኽችም ዛፍ በታች ዕረፉ…›› በማለት ተናግሯል፡፡ ‹‹በፊትኽ ሞገስን አግኝቼ›› ብሎ አንድነታቸውን፤ ‹‹ውሃ ይምጣላችኍ›› ብሎ የሦስትነታቸውን ምስጢር ገልጾአል፡፡

ይኽቺ አንድነቱ ሦስትነቱን ሳይጠቀልለው ሦስትነቱ አንድነቱን ሳይከፍለው በአንድነት በሦስትነት የሚመሰገን እግዚአብሔር የተገለጠባት ዛፍ፤ አንድነት ሦስትነት በጐላ በተረዳ ነገር የታወቀባት ከሦስቱ አካል አንዱ አካል እግዚአብሔር ወልድን በድንግልና የወለደች የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ መኾኗን፤ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ እንዚራ ስብሐት መጽሐፉ ላይ
....‹‹አንቲ ውእቱ ዕፀ ድርስ ዘለአብርሃም በርስአኒሁ
....ዘብኪ አጽለለ እግዚአብሔር በሥላሴሁ ››
(ለአብርሃው በእርጅናው ወቅት፤ እግዚአብሔርን በሦስትነት ያስጠለለብሽ የወይራ ዕንጨት አንቺ ነሽ) በማለት ሲገልጥ፤ ዳግመኛም በዚኹ መጽሐፉ፡-

...‹‹እንቲ ውእቱ ዕፀት ዘነበርኪ ጥቃ ኀይመት፣
...ዘብኪ አጽለሉ ሠለስቱ አጋዕዝት››
(ባንቺ ሦስቱ ጌቶች (ሥላሴ) የተጠለሉብሽ በድንኳን አጠገብ የቆምሽ ዕንጨት አንቺ ነሽ) በማለት በአንድነቱ ምንታዌ (ኹለትነት)፣ በሦስትነቱ ርባዔ (አራትነት) ለሌለበት አምላክ የሦስትነቱ የአንድነቱ ምስጢር መገለጫ የሥላሴ ማደሪያ መኾኗን መስክሯል፡፡