መምህር ኃይለ ማርያም ላቀው
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከትንሣኤ በፊት ያለውን አንድ ሳምንት ሰሙነ ሕማማት /የሕማማት ሳምንት/ በማለት ትዘክረዋለች፡፡ ሕማማት የሚለው ቃል “ሐመ፤ ታመመ” ከሚለው የግእዝ ግስ የወጣ ሲሆን የጌታችንና የመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕማምና ሞቱ የሚዘከርበት ሳምንት ነው፡፡ በሌላም በኩል ይህ ሳምንት ከአዳም እስከ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱሱ ክርስቶስ የነበሩ ነፍሳት በሲኦል የቆዩበት የአምስት ሺህ አምስት መቶ የመከራ፣ የፍዳና የኩነኔ ዘመን መታሰቢያ ስለሆነ የሕማማት ሳምንት የሚለውን ስያሜ አግኝቷል፡፡ እንደዚሁም ይህ ሳምንት “ቅዱስ ሳምንት” ይባላል” ከሌሎች ሳምንቶች ሁሉ የተለየ የከበረ ነውና፡፡ ምክንያቱም በዚህ ሳምንት በእያንዳንዱ ዕለት ስለ ፍጹም ፍቅር የተከፈለ የመሥዋዕትነት ሥራ ስለ ተሠራበት፣ የሰው ልጆች ደኅንነት ስለ ተፈጸመበት፣ መድኀኔዓለም ስለ እኛ ቤዛ ሆኖ ለመስቀል ሞት ታዛዥ ሆኖ ነፍሱን ስለ ካሠልን “ቅዱስ ሳምንት” ተብሏል፡፡ በተጨማሪም “የመጨረሻ ሳምንት” ተብሎ ይጠራል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም በሙዓለ ሥጋዌው ለፈጸማቸው የቤዛነትና የአርአያነት ተግባራት ፍጻሜ በመሆኑ ነው፡፡
በዚህ ልዩ በሆነ ሳምንት ካህናትና ምእመናን በነግህ፣ በሠልስት፣ በቀትር፣ በተሰዓትና በሠርክ ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመጓዝ ስለ ጌታችን ኢየስስ ክርስቶስ ሕማማተ መስቀል የሚያዘክረውን ምዕራፍ ከቅዱሳት መጻሕፍት በማንበብና በመጸለይ ሕማሙንና ሞቱን ያዘክራሉ፤ ቅዱስ ያሬድ በመጨረሻው ሳምንት በየዕለቱ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የተፈጸመውን ነገረ መስቀል በተመለከተ ያዘጋጀውን መዝሙር ይዘምራሉ፤ አብዝተው ስግደትን ይሰግዳሉ፡፡