በዲ/ን ዮሴፍ ይኩኖአምላክ
ኮናኔ በርትዕ÷ ፈታሄ በጽድቅ÷ የሆነው መድኀኒዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ጻፍት ፈሪሳውያንን በቋንቋቸው በዕብራያስጥ ቢያስተምራቸው “እንደ ሙሴ፡- ባሕር ከፍለህ÷ ጠላት ገድለህ÷ ደመና ጋርደህ÷ መና አውርደህ፣ እንደ ኢያሱ፡- በረድ አዝንመህ÷ ፀሐይ አቁመህ÷ እንደ ጌዴዎን፡- ፀምር ዘርግተህ ጠል አውርደህ፣ እንደ ኤልያስ ሰማይ ለጉመህ እሳት አዝንመህ ልታሳየን እንወዳለን” የሚል ጥያቄ በቀረበለት ጊዜ የሰጣቸው ምላሽ “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል÷ ከነቢዩ ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም፡፡ ዮናስ በዓሣ አንበሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ÷ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል፡፡ የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈረዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና÷ እነሆም ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ” የሚል ነው፡፡ ጻፍት ፈሪሳውያንን ምልክት ያስፈለጋቸው ዋነኛ ምክንያት በጌታችንና በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት ለማመን አልነበረም፤ ይልቅስ እንደ ዘማ ሴት ምልክት በምልክት እየተደራረበ ማየትን በመናፈቅ ነው፡፡