Thursday, January 17, 2013

ጥምቀት


በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ


በሰው ልጅ ዘላለማዊ ድኅነት ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው ሥርዓተ ጥምቀት ከሌሎቹ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን በቀዳሚነት የሚፈጸምና የማይደገም ሥርዓት ነው፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “አንዲት ጥመቀት” በማለት የሥርዓተ ጥምቀትን አለመደገምና አለመሠለስ ገልጦ ተናግሯል /ኤፌ.4፥5/፡፡ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ተመዝግቦ እንደሚገኘውና፥ የታናሽ እስያ ክፍል በሆነችው ቁስጥንጥንያ በ381 ዓ.ም. የተሰበሰቡ 150 የሃይማኖት አባቶቻችን “ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት ለሥርየተ ኀጢአት፣ ለኀጢአት ማስተሥረያ /ኀጢአትን በምታስተሠርይ/ በአንዲት ጥምቀት እናምናለን” በማለት የጥምቀትን አንድ መሆንና ኀጢአትን በደልን የምታርቅ፣ የምታስወግድ ስለመሆኗ በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ተመርተው ተናግረዋል፡፡ ሃይማኖታቸውንም ገልጠዋል፡፡

Friday, January 11, 2013

ጥበብ ዘየዓቢ እምነ ኩሉ ጥበብ ከጥበብ ሁሉ የሚበልጥ ጥበብ

ጥር 1 ቀን 2005 ዓ.ም. 
በዲ/ን እሱባለው

christmas 1
ከሰማይ በታች ባሉት ፍጥረታት ላይ በገዢነት የተሾመው የዕለተ ዓርብ ፍጥረት የሰው ልጅ በምክረ ከይሲ ተታልሎ ከፈቃደ እግዚአብሔር ፈቀቅ በማለቱ ሞትን ወደ ዓለም አስገብቷል፡፡ በዚህም የተሰጠውን ነጻነት በገዛ ፈቃዱ አሳልፎ ሰጠ በምትኩም ወደ ሰይጣን ምርኮኝነት እና ጽኑ አገዛዙ ፈጽሞ ሄደ፡፡

መፍቀሬ ሰብእ አምላካችንም እንደ ወጣን እንቀር ዘንድ ተቅበዝባዦች እንድንሆንም አልወደደም፤ ባማረ በተወደደ ቸርነቱ ጎበኘን እንጂ፡፡ ወኢኃደጎሙ ውስተ ኃጕል ለዝሉፉ በዕደ ሰይጣን - በሰይጣን እጅ እንደተያዙ ሊቀሩ  በጥፋት ውስጥ አልተዋቸውም እንዲል፡፡ ከነበርንበት ጉስቁልና ያድነን ዘንድ የሰይጣን ምክሩን ያፈረሰው በአምላክነቱ፣ በከሃሊነቱ፣ ከጌትነቱ ወገን በምንም በምን ድል አልነሣውም ወኢሞኦ በኃይሉ መዋኢት ወኢኃየሎ በክሂሎቱ ወኢበምንትኒ እምዕበዩ አላ በትሕትናሁ ወፍትሐ ጽድቁ በትሩፋተ ምሥጢር እንግዳ- እንግዳ በሚሆን ተዋርዶ(ትሕትና) በሠራው ሥራ ድል ነሣው እንጂ፡፡