Pages

Sunday, November 25, 2012

ሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ







          ......«ሐምሌ 22 ቀን 1928  ስምንት ወታደሮች በስተጀርባቸው ሃያ እርምጃ ርቀው ተንበርክከው በተንጠቀቅ ቆሙ። ወዲያው አዛዡ «ተኩስ» በማለት ትእዛዝ ሲሰጥ ስምንቱም ተኩሰው መቷቸው። ግን በስምንት ጥይት ሳይሞቱ ቀሩ። መሞታቸውንና አለመሞታቸውን ለማረጋገጥ ዶክተር ተጠራ። ዶክተሩም እንዳልሞቱ አረጋገጠ። ከዚያም ሌላ ወታደር በሦስት የሽጉጥ ጥይት ራስ ቅላቸውን መትቶ ገደላቸው። .........

1875 .. በሰሜን ሸዋ አገረ ስብከት ሰላሌ አውራጃ ፍቼ ከተማ ተወለዱ። ወላጆቻቸው ዕድሜያቸው ገና በወግ ለትምህርት ሳይደርስ ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም በመውሰድ ባሕታዊ ተድላ ለተባሉ መምህር አደራ ሰጧቸው። በዚያው ገዳም የንባብ ቤቱንና የዜማውን የትምህርት ደረጃዎች በሚያስገርም ሁኔታ በአጭር ጊዜ አቀላጥፈው በመጨረስ ገና በልጅነት የዕድሜ ደረጃቸው ሦስተኛውን የቅኔ ትምህርት ጀምረው በአጭር ጊዜ ሙሉ ቤት ተቀኙ። ይህንኑ የቅኔ ትምህርት ለማስፋፋት በምዕራብ ጎጃም አገረ ስብከት ወደሚገኘው የቅኔ ትምህርት ማዕከል ዋሸራ ተሻግረው ለመምህርነት የሚያበቃውን ትምህርት ፈጽመው አስመሰከሩ።

Thursday, November 22, 2012

ጾመ ነቢያት


ክርስቲያኖች ከእግዚአብሔር በጸጋ እንደተወለዱ በማመን ለእግዚአብሔር ያላቸውን ፍቅር ከሚገልጡባቸው ነገሮች አንዱ ጾም ነው፡፡ ጾም ፍቅረ መብዓ ከመሆኑ በተጨማሪ ታዛዥነትንና የገቡትን ቃል ኪዳን ጠባቂነትንም ማሳያ ነው፡፡ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር አርአያ ተፈጥሯአል፡፡ ኃጢአት ሠርቶ የእግዚአብሔር አርአያነቱን ቢያጠፋውም እግዚአብሔር ግን በአርአያው ሲፈጥረው ምን ያህል እንደሚወደው ማረጋገጫ ስለነበር በኃጢአት ሲወድቅም እንደወጣ ይቅር ሳይል ሊፈልገው መጣ፡፡ እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ሊፈልግ የመምጣቱ ተስፋ የተነገረበትንና ሱባኤ የተቆጠረበትን ዕለት ለማየት በመናፈቅ ከቀረበው መሥዋዕት አንዱ ጾም ነበር፡፡

ሰው በኃጢአት ቢወድቅም ፈጣሪው ሊያነሳው፤ ቢጠፋ ሊፈልገው እንደሚመጣ በተስፋ ሲጠብቀው ወልደ አምላክ ሰው መሆኑ የተረጋገጠ እውነት ነው፡፡ ስለዚህ አዳም የልደቱን ነገር በትንቢት መነፅርነት ሲመለከተው /በነቢያቱ ትምህርትና ስብከት/፣ በሚኖርበት ዓመተ ፍዳ የምሥጢረ ሥጋዌ  ብርሃን ከሩቅ ሲመለከተው ኖረ፡፡ ምሥጢረ ሥጋዌን በትንቢት መነፅርነት ማየቱም መከራውን እንዲቋቋመው የተስፋ ስንቅ ሆነው፡፡